የአላሙዲ ኪስ በወርቅ ሲታጨቅ፤ አዶላ ኑሮ በጭንቅ!

(አሥራደው ከፈረንሳይ)

gold

October 25, 2012 02:16 am By  Leave a Comment

ከሳምንታት በፊት የለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ ድራማ!! ወርቃችን እንዴት አላሙዲ እጅ ገባ? በሚል ርዕር ላቀረብነው ጽሑፍ የድረገጻችን አንባቢ አሥራደው የሚከተለውን በግጥም የተከሸነ መልዕክት ልከውልናል፡፡

ተናገር መጋዶ ተናገር ሻኪሶ፤
ወርቅ ወዴት ተጋዘ ላንተ አፈሩ ደርሶ፤
ተናገር ሃዲማ ደግሞም ኡላኡሎ፤
እነማን ዘረፉት የወርቁን አሎሎ?!
የወርቁን ቡችላ የለገ ደንቢውን፤
ደብዛውን ንገሩን የደረሰበትን?!

እነማን ዘረፉት ? ማንስ ከበረበት?!
እነማን ተዝናኑ? ማንስ ጨፈረበት?!
ድሃ በደከመ ድሃ በሞተበት፤
ጦሙን እንደዋለ አፈር ተንዶበት::

አካፋና ዶማ ይዘው ሳይቆፍሩ፤
ጨለማ መግፈፊያ ሻማ ሳያበሩ፤
ጠብ ሳይል ላባቸው ባቋራጭ ከበሩ፡
ያገር አንጡራ ሃብት እየመዘበሩ::

በገዛ መሬቱ በተወለደበት፤
ዕትብቱ ተቆርጦ ለተቀበረበት፤
ለወርቁ ባለቤት ምንም ሳይሰሩለት ፤
ጉሮሮውን አንቆ ካፉ በመቀማት፤
ሃብታም መዘበረ ባዳ ከበረበት::

አወይ ክብረ መንግሥት እንዴት ነው አዶላ?!
ድሃን እያስራበ ሃብታም የሚያበላ!

ግብግብ፤ የህይወት ትንንቅ፤ በመኖርና ባለመኖር መሃከል የሚደረግ የህይወት ፍትግያ፤ በፍትግያው መሃከል በሚፈጠረው የሕይወት ሙቀትና ብልጭታ፤ የሰውን ልጅ አካል በደስታ አሙቆ፤ ብርሃን በመፈንጠቅ ነገንና ተነገወዲያን ወለል አድርጎ የሚያሳይ የማንነት መስታወት ::

የሰው ልጅ ዘር ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘን ተሰባስቦ፤ የሕይወት ሀ ሁ ቆጥሮ፤ አቡጊዳን በመማር፤ የሕይወትን መጽሐፍ ለማንበብ እንዲችል የተሠራች የሕይወት ትምህርት ቤት አዶላ!

ከየ ክፍላተ ሃገሩ የሕይወት ገመድ ጎትቶ ባመጣቸው ልጆቿ፤ የእናት አገራችን ኢትዮጵያ ከርሰ ምድር፤ በአካፋና በዶማ እየተማሰ፤ አፈሩ በእንቅብ እየታፈሰ፤ በገበቴ ላይ ሆኖ በውሃ አዋላጅነት አከላቱን ታጥቦ፤ ዓይኑን ኩል ተቀብቶ፤ የጣር ልጅ የሆነው ወርቅ የሚወለድባት ምድር አዶላ!

እህ ! እህ ! እህ ! ይህ ድምጽ፤
በጉድጓዱ ውስጥ ሆኖ የሚቆፍረው ሰው ለቁፋሮ ዶማውን ሲሰነዝር፤ በያንዳንዱ የእጅ ንዝረት መሃል የሚያሰማው ድምጽ ነው::

እህ ! እህ ! እህ ! እያንዳንዱ የእጅ ንዝረት በዚህ የጣር ድምጽ ይታጀባል፤ ዶማው የጉርጓዱን ግርግዳ እየገመሰ ሲጥል፤ እድም ! እድም ! እያለ የሚያስተጋባው ድምጽ ደግሞ ለጀግና የሚመታ ከበሮ ይመስል ድፍረት ይሰጣል፤ ከቆፋሪው ሰውነት ላይ እንደ ምንጭ የሚፈልቀው ላብ ገላውን አቋርጦ ሲወርድ፤ አፉን የከፈተው ጉርጓድ በሱ ጥማት ጥሙን ይቆርጣል፤ ጭል ጭል የምትለው ሻማ ትንፋሽ አጥሯት በመጨነቅ ስቅስቅ ብላ  በማልቀስ ስሞታ ታሰማለች ::

አንዱ ሲቆፍር፤ ሌላው አፈሩን እያፈሰ በጉርድ በርሜል ውስጥ ይሞላል፤ በርሜሉ ጢም ብሎ ሲሞላ፤ ከውጪ በተቸከለ እንጨት ላይ ገመዱን ጠምጥሞ ለሚጠባበቀው ጓደኛቸው በርሜሉን እንዲስብ በፉጨት ምልክት ይሰጡታል፤ በዚህ መልክ አፈሩ በገመድ በታሰረው ጉርድ በርሜል ላይ ተጭኖ ከጉርጓዱ ይወጣል:: ከአፈሩ ጋር ሆና በቀጭኑ ገመድ ላይ ሕይወት አብራ ትወጣለች ትወርዳለች፤ ወርቅ ሕይወት ናት፤ ሕይወትም ወርቅ ናትና::

አየሁሽ! አላየሁሽ! የሰው ልጅና ወርቅ በአፈር ውስጥ ሆነው የሚጫወቱት የድብብቆሽ ጫወታ!!

በዚህ የህይወት ድብብቆሽ መሃከል ድንገት እቀጭ የሚል ድምጽ ይሰማል !
ቡችላው ነው ?! … ቡችላው ያስደነግጣል፤ በርግጥ እቀጭ! ያለው እሱ ከሆነ::
የደስታ ድንጋጤ፤ የድካም ውጤት ማብሰሪያ ቃጭል !
በላብ ተቦክቶ፤ ከሰውነት ግለት በሚወጣው እንፋሎት፤ የተጋገረ ትኩስ እንጀራ፤ የአብሮ መብላት አምላክ፤ አብረው ለተራቡ ነብሶች የሚሰጠው ህብስተ መና ::
የዕድልና የልፋት ግጥጥሞሽ !

ቡችላው ማነው? ለምንስ ቡችላ ተባለ?
እሽሽሽ ! … የአዶላ ልጆች!  ከተነሳሁበት ርዕስ ጋር መልሱን እንዳመቸኝ ይዤ ብቅ እላለሁ::

በወርቅ ቁፋሮ በተሰማሩ ወገኖቼ ላብ እያጠቀስኩ የጨነቆርኳት በመሆኗ፤ በአዶላ የወርቅ ማዕድን፤ በቁፋሮ ሥራ ለተሰማሩ ወገኖቼ ማስታወሻ ትሁንልኝ ::

ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም. (October 17/2012)

 

Advertisements

Posted on November 20, 2012, in Human Right and tagged , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s