የመሸ ዕለት… ቀኑ – ከሥርጉተ ሥላሴ

ከሥርጉተ ሥላሴ 21.11.2012

መደበኛ ተግባሬን ልከውን አስቤ እርማት ጀምርኩ። ግን መቀጣል አልቻልኩም … ዕንባ ተናነቀኝ። ሰሞኑን ደግሞ በጣም ያባባኛል። ባር – ባርም ይለኛል። ሳስበው ይሰቀጥጠኛል።  ከእእምሮዬ አልወጣ አለ። ይቀመጥ -ፈቅጀለታለሁ። ደራ ወረዳ የተፈጸመው „የኦሾቲዝም“ ሚስጢር ዓይነት ኢ-ሰባዕዊ ቃሉም አይገልጸውም። ሰቅጣጭ ድርጊት ቀልቤን ፈተለውና ውስጤን ላጋራችሁ ብዬ አሰብኩ። የጀመርኩትን አቋርጬ እንሆ …. እርእሱ …

አሉታዊ ዕለታት ….. ሲደረደሩ።

ዕለት ዓለት የሚሆንበት ገጠመኝ አለ። ዕለት በረዶ የሚሆንበት ዕለት አለ። ዕለት ሸክም የሚሆንበት ዕለት አለ። ዕለት ዕዳ የሚሆንበት ዕለት አለ። ዕለት ድብርት የሚሆንበት ዕለት አለ። ዕለት ደመመን የሚሆንበት ዕለት አለ። ዕለት ሲቀፈው ለዕለቱ ባልወለድ አንጀቱ ይጭነዋል። ዕለት ተዝቅዝቆ የሚጠራችሁ ዕለት አለው። ዕለት ታገድሞ የሚጠራችሁ ዕለት አለው። ዕለት በጎሪጥ የሚያችሁ ዕለት አለው። ዕለት ተጎንብሶ የሚሟጥጣችሁ ዕለት አለ።

ዕለት አፈር እዬነፋ የሚያሳያችሁ ዕለት አለ። ዕለት ጎርፍ ልኮ የሚናውጻችሁ ዕለት አለ። ዕለት ዓውሎ አሳዝዞ የሚሰቅዛችሁ ዕለት አለ። ዕለት ተስፋ ቆራጭነትን የሚልክባችሁ ዕለት አለ። ዕለት የሚስቅባችሁም ዕለት አለ። ዕለት የሚሳላቅባችሁም ዕለት አለ። ዕለት ቀድሞ ትቢያ የሚያለብሳችሁም ዕለት አለ።

አዎን ዕለት ገና ከመምምጣቱ ቀድሞ ፍርኃትን የሚለግሳችሁ ዕለት አለ። ዕለት ሳትፈጠሩ የሚቀብራችሁም ዕለት አለ። ከሁሉ የከፋው ዕለት ይሄ ነው ሳትፈጠሩ ስትቀበሩ። ደራ ወረዳ ላይ በአንድ ንጹህ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ህዳር 8 ቀን 2005 ዓ.ም በደረሰው ግፍ የ6ወር ጽንስ ሳይፈጠር በጭካኔ ይሙት በቃ ተፍርዶበታል።

ወገኖቼ … ዜናውን ያዳመጣችሁ ዕለት ያን ቀን ከቶ ከእህል እውኃ ጋር ተገናኛችሁን? አንቅልፍስ ወሰዳችሁን? ልጆች ያላችሁስ ምን ተሳማችሁ? ጽንስ በሆዷ ያላት ሚስት፤ እህት፤ እናት፤ አክስት፤ ያላችሁስ ህሊናችሁ – ስሜታችሁ –  መንፈሳችሁ ከቶ ምን አላችሁ? በምንስ ተሰማማችሁ? ደግ ነው ወሸኔ አላችሁን?¡¡  … ወይንስ እረመጡ አንገበገባችሁ? ያ አሳዘኝ ዜና .. በፍል ቁጭት መቀቀሉስ አረፍት ሰጣችሁን? ሀዘን ላይ አልተቀመጣችሁም? ኢትዮጵያዊነታችን አልጠያቃችሁትንም? እሱስ አልተዬቃችሁንም? ይህ ሙጃ ወያኔ መራሽ አስተዳደር እንደ ጥንቸል በዬጊዜው ቤተ – ሙከራ በወገኖቻችን ስለ ማድረጉስ አልጎረበጣችሁንም?

በዬትኛውም ዘመን፤ በዬትኛውም ሁኔታ ታይቶ ተስምቶ በማይተወቅ ሁኔታ በደራ ወረዳ መሳሪያ ደብቀኃል የተባለ ንጹህ ገበሬ ብልቱ በገመድ ታስሮ የስድስት ወር ነፍሰጡር ሚስቱ በጥርሷ ገመዱን እዬጎተተች መሳቂያና መሳለቂያ እንድትሆን ተፈረደባት። እሪ! እሪ! እሪ! እሪ! .. ያልሳቁት ተደበደቡ የሳቁባት ደግሞ ተደነቁ … ኡ ኡ ኡኡ ኡ ኡ …

በመጀመሪያ ነገር ኢትዮጵያ የራሷ ማንነት ያላት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ህግ ሀገር ናት። በመሆኗም ለማናቸውም ክስተት ተፈጥሯዊ ሥርዓት፤ መተዳደሪያ ህግ፤ የአፈጻጸም መመሪያ ያላት ሀገር ናት። ከሁሉም በላይ የፈርኃ እግዜአብሄር ቤተ- መቅደስ ናት።

በሀገራችን በኢትዮጵያ ጋብቻን አስመልክቶ በሦሥት መልክ ይፈጸምባታል። ሃይማኖታዊ፤ ባህላዊና ብሄራዊ በሆነ መልኩ። ከዚህ ጋር መንግሥታዊ በሆነ መልኩ ለአፈጻጻሙ የፍትኃብሄር ሥርዓት ሕጉና መቅጫው ፤ የወንጀለኛ ሥርዓት ህጉና መቅጫ አሉ። ሃይማኖታዊ በሆነ መልኩም ቀኖናም ዶግማ እንደ አግባባቸው ተግባር ላይ ይውላሉ።

ባህላዊ ጋብቻን በሚመለከትም በሀገር ሽማግሌ ማህበረሰቡ ፈቅዶና ወዶ በተቀበላቸው ሥርዓት ጋብቻ ይመራል። ይዳኛል። በጋብቻ ሂደት የሚፈጸሙ ማናቸውም ግንኙነቶች ወግ አላቸው። ወግ የልማድ ተግባርት እንዳይጣሱ ሥርዓት የሚያስከብር የባህል አካል ነው። እንደ ሥርጉተ ዕይታ ወግ የባህል ወታደር ነው።

ኢትዮጵውያን  በዬትኛው ዓለም ቢኖር ከዚህ ሥርዓት ውጪ ሆኖው አያውቁም። ከሀገራቸው ትውፊታዊ ዕሴቶች ፈቀቅ አይሉም። በፍጹም። በሥነ -ጥበብ ዘርፍ እንኳን አፈጻጸሙ፤ ደስታ ሰጪነቱ ቅኔያዊ ነው። በሥነ ቃል የተዋበ እንጂ ደፍሮ እንኳን በዛ ዙሪያ ያሉትን አካላት እንደ አንገት፤ እንደ ልብ፤ እንደ ሳንባ፤ እንደ ኩላሊት በቃል አፉን አውጥቶ የሚናገር ፈጽሞ በእኔ ዕድሜ አላዬሁም።

እውነት ለመናገር በአንዳንድ አካባቢ ያደግንም ሰዎች ሙሉ ዕድሜ ላይ ሁነን እንኳን የተቃራኒ ጾታ ፊልሞችን ዓይናችን በፍጹም ደፍሮ አያይልንም …  በሥነ – ጥበብ ህግጋት ሥርዓትና ደንብም የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሲኖሩ ወይንም አስፈለጊ ጹሑፎችን ስንጽፍ አጋድመን በቃላት ሸፈን – ከደን አድርገን ሃምሳ ክንዱን አጎናጽፈን ነው የምንጽፈው …

ይህ የአረም የአረነዛ በቀል ያወረዛ ዘመን ግን ስንቱን የውስጣችን ገላጭ ትውፊት እደሚረግጥ ተመልከቱት … ግፍ አይገልጸውም፤ በደል አይገልጸውም፤ ጭቆና አይገልጸውም … የመዳህኒታችን  የእዬሱስ ክርስቶስ ሥነ – ስቅለት ዳግማዊነት … ዘመነ ህማማት …

እንዴት ይሰቀጥጣል? እንዴትስ ይከፋል? እንዴትስ ይመራል? እንዴትስ እንደ ሃሞት ይጎመዝዛል። እንዴትስ ሆድ ያስበሳል? እኛ ምንድንነን ሰው ነን -ን? ዜጋ ነን-ን? ከዬት ተፈጠርን? እንዴት ተፈጠርን? መቼ ተፈጠርን? በአካላችን እንዲህ መሆን ምን ይሰማናል?

በደሉ ስንት ነው? በምን ስሌት በምን ቀመር ይገለጻል? ይህቺ ምስኪን ፍጡር ነገ እንዴት ነው በሙሉ ሰውነት እንደ ሰው ከሰው ጋር በዬትኛው የሞራል ጥሪት ነው የምተቀላቀለው። … እንዴት ልትኖር ነው ከዛ አካባቢ? በዬትኛው የሞራል ጉልበት ነው ቀጣይ ሕይውቷ የለመደውን አታካች ኑሮ የሚገፋው …? ባለቤቷስ እንዴት ብሎ ነው ተፈጥሯዊ ሰብዕናው እንደ አንድ ሙሉዑ ተባዕታዊ ሥነ -ሕይወት የሚቀጥለው …?

ገና ያልተፈጠረው በጽንስ ላይ እያለ ለሞተው የትውልድ ዕንቡጥ ማን ነው ጠበቃው? ማነው ዋቢው? ማን ነው ሁነኛው? ስለ ሰባዕዊ መብቱስ ማን ነው የሚጮኽለት? … የህጻናት ዓለም ምን ይላል? ለመሆኑ በጽንስ ላይ እያሉ በግፍ እንዲሞቱ ስለሚፈረድባቸውስ ለማን ነው አቤቱታ የሚቀርበው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ሰባዕዊ መብት ተረገጠ ሲባል ጽንስ፤ ጽንስን ሊፈጥሩ የሚችሉ አካላት እኮ ጭምር እኮ ነው የተባእቱም፤ የአንስተቱም ፍሬ ሰጪ አካላት ነው በግፍና በማናለብኝነት የተቀጠቀጡት … እግዚኦ! እግዚኦ! እግዚኦ!

… ይህ እኮ የረቀቀ ረመጥ ነው … እንዲህ ለሚያደርግ መንግስት ነው በተባበሩት መንግስታት የሰባዕዊ መብት አስከባሪነት ኮሚሽን አካልነት  ቦታ ወንበር የሚሰጠውን? በምን መስፈርት …? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከጽንስ ጀምሮ ሞት በጠራራ ጸሐይ የሚፈረድበት ሰው አይደለም ወይንስ ምንድን ነው? … በእውነቱ እኔ አልገባኝም …

ዘመነ አራዊት፤ ዘመነ ሳጥናኤል፤ ዘመነ ጭራቅ፤ መቼ ይሆን  በኢትዮጵያ የሚያከትመው? ቀን አለውን? ይህ የቋሳ ዕለታዊ ሕይወት ቀጠሮ ይሰጣልን? …

ፈጠሪ አምላክ እባክህን አትዘግይ? ከጽንስ ቅጣትስ ወዲያ ምንስ ይምጣ? ብዙ ተባዙ ብለህ የመረቅኽው አንደበትህ እኮ ተጠቀጠቀ፤ ተ  ጨ  ፈ ለ ቀ   እኮ! አንተ የሁሉ ጌታ እስከ መቼ ለበለኃሰብ ጊዜ ትሰጣለህ? ቁጣኽን እዘዝ — እየመነጠረ እንዲመለምል … አንዲያከስምም … ብን አድርጎ  እንዲያትን ወይንም እንዲበተን … ሁሉ በእጀህ ነው ምን ይሰንኃል? እባክህን የኔ ጌታ ጉልበት ስጥ ለደም ዕንባ ኃይላችንን አትረፍርፍ –  አጠንክር። ለተጋፋ – ለተረገጠ  -ለተጨቆነ ብዙኃን ህዘብ … ሥጦታህን በውጤት አቁርበው እባክህን?! ኧረ እባክህን!?!

አምላካችን ሀገራችን በምህረት ዓይኑ ይጎብኝ! አሜን

ECADF.COM

Advertisements

Posted on November 22, 2012, in Human Right and tagged . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s