ኃይለማርያምን ፍለጋ

ከሰለሞን ስዩም

በተለያዩ ጊዜያት ስለጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ፅፌያለሁ፡፡ ይህን ያደረግሁት ስለ ሰውዬው መከታተል ከጀመርኩ ከረዥም አመታት በኋላ ነው፡፡ ጠ/ሚ/ሩ ወደ ስልጣን ከመጡ ከረዥም አመታት በኋላም፡፡ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊትማ እንኳን እርሳቸውን ራሴንም አላውቅም ነበር፡፡ ስለ ጠ/ሚ/ር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ለመሞገት ግን እድል በእጄ ላይ ጥላቸዋለች፡፡ ሰውዬውን ከደቡብ ብሔረ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዚዴንትነታቸው ጀምሮ ስለማውቃቸው፡፡ በነገራችን ላይ ስለ ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊና ኢህአዴግ ሙሉ ሀተታ የያዘ ወጥ መፅሐፍ (አሁን እንደተለመደው ጋዜጣ ላይ ከወጡ ፅሁፎቼ የተወደ አይደለም) በቅርብ ቀን እንደማስነብባችሁ ቃል እየገባሁ ለዛሬ በተወሰነ መልኩ ብቻ ከኃ/ማሪያም ጋር እያወዳደርኩ ካልሆነ ትኩረት አላረጋቸውም፡፡

አቶ መለስ ሀሳባቸውን በመግለፅ አይታሙም፡፡ ሀሳባቸው ግን ከራሷ ግዛት ውጭ የሆኑትን ነገሮች በግድ ለመጠቅለል የምትጥር ነበረች፡፡ የመለስ ሀሳብ አብዛኛውን ጊዜ መሬት ካለው ነገር የበዛ ነበር፡፡ ይህ ማለት ጀርመናዊው ፈላስፋ ሄግል ‹‹በሀሳቤና ሀሳቤ በቆመለት ነገር መካከል ያለውን ልዩነት›› በማለት ለማስታረቅ ካደረገውን ጥረት በተቃራኒ ማለት ነው፡፡ አቶ መለስ ሀሳባቸው መሬት ካለው ነገር አልፎ የሚሄደው በሁለቱ መካከል (በሀሳቡና እውነታው) መካከል ያለው ልዩነት ባብዛኛው ወደሀሳቡ ስለሚያደላ ነበር፡፡ ሆኖም ግን፣ ሰውዬው ይህንንም ለማድረግ ብዙ ማሰባቸው ስለማይቀር የዘመናዊ ፍልስፍና አባት የሚባለው ዴካርተስ “I think hence I’m” ያለውን የሚያሟላ ይመስላል፡፡ ዴካርተስ “ስለማስብ እንዳለሁ አረጋገጥሁ” ያለው ቁምነገር በአቶ መለስ እና ተከታዮቹ ዘንድ ግን ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡

ኢህአዴግ በፖሊሲዎቹ ሁሉ ቁሳዊ ልማት የማረጋገጥ ጥረት ላይ ያጠነጥናል፡፡ የኢህአዴግ ፖሊሲ በተቻለ መጠን ሰዎች በልተው ስለማደራቸው ብቻ እንዲያስቡ የሚያትት ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ በልቶ ስለማደር መወትወት መልካም ነው እንኳ ብንል መንገዱ የተበላሸ ይመስለኛል፡፡ ሊረጋገጥበት የሚችለው ጥራት ያለው ትምህርት ሲኖር ነውና፡፡ ኢህአዴግ ግን ‹‹እንብላ›› የሚለው የትምህርትን እናት ቀብሮ ነው፡፡ “የሰው ልጅ የሚያጠነጥነው በሆዱ ዙሪያ ነው” የሚለው ካርል ማርክስ የኢህአዴግን ፖሊሲ ተንብዮ መሆን አለበት፡፡ አሊያም መለስ/ኢህአዴጎቹ በሰውዬው ሀሳብ ከመጠን በላይ ተመስጠዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት አቶ መለስ ከላይ ያሰፈርነውን የዴካርተስ “I think hence I’m” ሲያነብ “I eat thus I’m” (በልቼ ስለማድር መኖሬን አረጋገጥኩ) ብሎ ነው ማለት ነው፡፡ እኔ ግን መብላት የመኖር ትርጉም ነው አልልም፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን፣ ብሉይ ቢሆንም “I’m certain that I’m, because I think” ብል ይቀለኛል፡፡ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እንደ መለስ ዜናዊ በቃላት አይጫወትም፡፡ በቃላት መጫወት የምለው ልክ እንደ ሶፊስቶች አሊያም ዲያሌክቲስቶች የቃላት ሰርከስ በመስራት ለእውነት ግን ግድ ማጣትን ነው፡፡

አቶ መለስ አንድ ከተሰጣቸው ዓረፍተ ነገር አሊያም ራሳቸው ከሰሩት ዓረፍተ ነገር (premise) ሌሎችን እያራቡ በመጨረሻ የመጀመሪያውን ዓረፍተ ነገር የሚቃረን ሀሳብ ጋር ሊወስዱን የሚችሉ መሪ ነበሩ፡፡ በከፍተኛ ምክንያታዊነት የደረሰበት የሚመስለው የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር ግን የእውነቱ ተቃራኒ ነው፡፡ ይህ የ ‹‹Dialectics›› ጥበብ ነው፡፡

ሶፊስቶች ደግሞ አሉ፡፡ ሶፊስቶች እንጀራቸውን የሚያበስሉት ምክንያታዊነትን ያለ አግባብ በመጠቀም ነው፡፡ አግባብ ያልሆነ አመክኒዮ በመጠቀም እውነትን በማድማት ኑሯቸውን የሚመሩ ናቸው፡፡ አሊያም ደግሞ የተሰጣቸው ደረጃ፣ ደረጃውን ለሰጧቸው ቡድኖች እውነትን ባደሙላቸው መጠን ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ሲያደርጉ እውነተኛ ለመምሰል በቃላት ጨዋታ የተካኑ መሆን አለባቸው፡፡ የግላቸው ዋና አላማ ደግሞ በየትም ብለው የተመኙትን ቦታ መያዝ ነው፡፡ እነዚህን ለመዋጋት ፍልስፍና እንደጀመረ የሚነገርለት ታላቁ ፕላቶ የሶፊስቶችን መንገድ “unreal wisdom” /እውነተኛ ያልሆነ ጥበብ/ ይለዋል፡፡

የመለስ ዜናዊ እንጀራ ስልጣን ላይ ረዥም ጊዜ ለመቆየት ከሆነ ሶፊስትም ነበሩ ልንል ነው፡፡ ኃ/ማሪያም ግን ሶፊስትም ዲያሌቲክስትም ሳይሆኑ እንደምን የመለስ አልጋ ወራሽ ሆኑ? ይህ ማለት ኃ/ማሪያም ለእውነት የቆሙ ናቸው ብዬ አይደለም፡፡ ይልቅ እንደ መለስ የቃላት ጫካ መሃከል ሳይደበቁ በግልጽ እውነትን ስለሚያጠቁ ብዬ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ንግግር አዋቂ ናቸው እንላለን፡፡ ‹‹እውነት›› አዋቂ ግን አልነበሩም፡፡ ንግግርም እውነትም የማያውቁት አቶ ኃይለማሪያም ታዲያ እንዴት ለመለስ ተተኪ ሆኑ ነው ጥያቄዬ፡፡

የዛሬ አላማዬ መጠየቅ በመሆኑ ያለ መልስ እቀጥላለሁ፡፡ አቶ ኃ/ማሪያም የኢህአዴግ ፕሮግራም ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር ይመሳሰላል ሲሉ ክርስትና ሊሰብኩን የሞከሩ እለት “እውነት እኚህ ሰው ኢህአዴግን ያውቃሉ?” ብያለሁ፡፡ አንድ አብነት እንኳ ባነሳ የኢህአዴግ /ህወሓት ህገ መንግስት ሰዎችን በብሔራቸው፣ በብሔረሰባቸው አሊያም በህዝባቸው በኩል ካልሆነ እንደማይቀበል ሳያውቁ በእንደምን ጠ/ሚ/ር ሆኑ እላለሁ፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ በክርስትና መስፋፋት ላይ ስኬት ያገኘው ሰዎችን ከቡድናቸው ውጭ እኩል በማየቱ ነው፡፡ ኃ/ማሪያም ግን የመንግስታቸው ህገ መንግስት መግቢያ የሚለውን ሳያነቡ (ቢያነቡ ያንን አይሉም ነበር) ጠ/ሚ/ር መሆናቸው እንቆቅልሽ ይሆንብኛል፡፡ መግቢያው “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች . . .” ከማለት የዘለለ “በምርጫዬ ኢትዮጵያዊ ነኝ” የሚለውን ክላውድ ሳምነር፣ ህይወቱን ሙሉ ኢትዮጵያን ያገለገለውን ሪቻርድ ፓንክረስት . . . አያጠቃልልም፡፡ “ዘሬ ክርስቶስ ነው” የሚለኝ ፕሮቲስታንት ጓደኛዬን ‹‹ከመፅሐፍ ቅዱስ ጋር ይመሳሰልብኛል›› የሚሉት የኢህአዴግ ፕሮግራም የት ያውቀዋል? ኃይሌ የኢህአዴግን ፕሮግራም እንደማያውቁ ግን መልስ አግኝቻለሁ፡፡ መልሴንም መጠየቅ (quesstion) ብትችሉም ቅሉ፡፡ “አንድን ነገር” ማወቅ ምንነቱን መተንተን፣ መዘርዘርና መናገር ነው፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ሰዓት “አንድ ነገር” ምን እንዳልሆነ መተንተን፣ መዘርዘር እና መናገር ይጠይቃል፡፡ በዚህ መስፈርት መሰረት ኃ/ማሪያም ኢህአዴግ ምን እንደሆ እንጂ ምን እንዳልሆነ አያውቁም፡፡ ይህ ሌላኛው ገጽ ዋነኛው የኢህአዴግ ገጽ ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ያለመሆኑ፣ ክፍት ያለመሆኑ፣ ሆደ ሰፊ ያለመሆኑ፡፡ ማወቅ ግልጽና ልዩ (clear & distinct) የሆነ ፀባይ መተንተንን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማሪያም ኢህአዴግን አያውቁም፡፡

ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለሀ/ማሪያም ስለ ኢህአዴግ ብዙ ነገር ይነግሯቸው ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ጠ/ሚ/ር ኃ/ማሪያምም ያለ መጠራጠር እንዳሉ ይውጧቸዋል፡፡ ይህን ለምን ያነሳሁ መሰላችሁ፡፡ ዴካርቴስ ‹‹ከማሰቡ›› በተጨማሪ ሁለተኛው የመኖሩ ማረጋገጫ ያደረገው ‹‹መጠራጠሩን›› ስለነበር ነው፡፡ ዝም ብሎ መስማትማ እንስሳትም ይሰማሉ፡፡ አይመርጡትም፣ አይጠረጥሩትም፡፡ ይህ አርስቶትል “Animals are true machines” ብሎ ከዘረዘረው ከግዑዝነት ትንሽ ብቻ ከፍ ማለት መስፈርት ጋር ይጣጣማል፡፡ እንስሳት የሚመጣውን መረጃ /ሁነት ከማስተናገድ ውጭ የገባውን አያመዛዝኑም፣ አይሰልቁም፡፡ የገባውን ሁነት ካላመነዠኩት እንደሚያስቡ እንዴት እናረጋግጣለን?

ለሰው ግን እንዲህ መሆን ባልተገባው፡፡ የኃ/ማሪያም ሁሉን መዋጥ ግን መጠራጠሩንና ማሰቡን እንድጠራጠር አድርጎኛል፡፡ ታላላቆቹ የሀሳብ ሰዎች “A mind can’t cease to think unless cease to be”/አዕምሮ መኖር(መሆን) ካላቆመ ማሰብ አያቆምም / ከሚለው ሀሳብ ጋር እየተጣረሰብኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው “እውን ሰውየው አሉ?” ስል ፍለጋ የጀመርኩት፡፡ እውን ሰውየው አሉ?

 

ETHIOPIAN MEDIA FORUM.COM

Advertisements

Posted on November 28, 2012, in Politics and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s