ድንጋይን የሚያናግረው ውኃ ነው!

ክፍል-፩

ድንጋይን ለብዙ ጉዳዮች ምሳሌነት እንጠቀምበታለን፡፡ የማይንቀሳቀስን ነገር ለመግለጽ “እንደ ድንጋይ ተጎልቶ” እንላለን፡፡ ቀለም ወይም ሐሳብ በአእምሮው መንሸራሸር ያስቸገረዉን ለመዝለፍም “ድንጋይ ራስ” ስንል እንገኛለን፡፡ የሰዉን አስተዋይነት፣ ታጋሽነት፣ ጨዋነት ለማንጸባረቅም “እንደ ድንብልዝ የረጋ፤ እሱማ ድንጋይ አይደል! አይናገር” እንላለን፡፡ ትክክል ይሁንም አይሁንም መቸም እስካሁን ድረስ በኛ ወገኖች ዘንድ ዝምታ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ዉስጥ ድንጋይ የመጨረሻዉን ትርጉም ይይዛል፡፡

በቤተ-ክህነት የሓዲስ ኪዳኑ ተርጓሚ፤ ሊቀ-ሊቃዉንት መሐሪ ትርፌ (በኋላ አቡነ ጴጥሮስ)፣ የሃይማኖት እዉቀት መጠንሰሻና መጥመቂያ ጋኑ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ፣ የእምነት ፈላስፋውና የብዙኃን ቋንቋ ሊቁ ሰማእቱ አቡነ-ቴዮፍሎስ፣ የቤተ-ክርስቲያን እዉቀት አባቱ አቡነ-ጎርጎሪዮስ ወዘተ ደንጋዮች ነበሩ፡፡ ቀለምን ብራናና ወረቀት ላይ እንዲያንጠፈጥፉ ያደረጋቸው የዉኃ ሐይል ነዉ፡፡ በሥነ-ፅሑፍ የኢትዮጵያ አባቶች የሆኑት ሀዲስ አለማየሁና ከበደ ሚካኤል፣ ተከላካያችን ፀጋዬ ገብረ-መድህን፣ ግዞትም ሞትም ያላሸነፈው አቢ ጉበኛ፤ የሕዝብ ችግር በመናገሩ ህይወቱን ያጣዉ የሕዝብ ልሳኑ ባህሉ ግርማ ወዘተ ድንጋዮች ነበሩ፡፡ አዎ ከድንጋይም ደግሞ ወፈጥ! እነዚህንም ያልተመቻቸ ኑሮ እየኖሩ በገዥዎች እየተንገላቱ፣ እየታሰሩ፣ እየተገረፉ፣ እየሞቱም እንዲናገሩ ያደረጋቸው ይኽው ዉኃዉ ነው፡፡ እንደ አቤ ጉበኛና ባህሉ ግርማ በአረመኔዎች ትእዛዝ ወይም እጅ ሳይሆን በሌላ መልክ የተለዩን የሀዲስ አለማየሁና ከበደ ሚካኤል ህልፈት በእድሜ፤ የፀጋዬ ግብረ-መድህን መለየት በኩላሊትና በልብ በሽታ ተመካኘ እንጅ በእዉነቱ የዉኃ እጅም አለበት፡፡ የሚያናግር ዉኃ መልክ መልክ አለው፡፡ አንዳንዱ የዉኃ ዓይነት ወደላይ እያጓነ በደስታ ያናግራል፡፡ ሌላው ዓይነት ደግሞ ከላይ ሆኖ እየደቆሰ ያስተክዛል፤ ያስቆዝማል፡፡ እንዲያም ሲል ይገላል፡፡ እንደአለመታደል ሆኖ የኛዎችን የቀለም አባቶች ባብዛኛው ሲያናግራቸዉ የኖረው፤ በመጨረሻም ይዟቸዉም የሄደው የኋለኛው አይነት ዉኃ ነበር፡፡

“ጋኖቸ አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ” ይሉ ነበር አበዉ ሲተርቱ፡፡ እኛስ መቸም እንኳን ፍልስፍና ያዘለ ተረት ልንፈጥር የተፈጠረዉንም መጠበቅ አቅቶናል፡፡ ለነግሩ ዛሬ ዛሬስ  እንኳን ጋኖች ምንቸቶችም ያለቁ ይመስላል፡፡ ከዚያም አልፎ እንስራው፣ ቻቹ፣ ጀበናዉና ሌላ ሌላዉም የተከበረዉ ያገር ሐብት ከፊሉ በዘነዘና እየተደቆሰ አለቀ፡፡ ሌላውም የደረሰበት አልታወቅ አለ፡፡ የቀረዉም በተፈጠረባት ምድር በገመድ ተጠፍሮ በመማቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ታዲያ የጋን፣ የምንቸትና የሌሎችም መመንመን ለአዉደልድልና ለማንቆርቆሪያ እጅግ ጠቅሟል፡፡ አዉደልድል ከሰፈር ሰፈር ሲላላክ፤ ማንቆርቆሪያም ባፉ ያስገቡበትን ሁሉ በፉርፉርቱ እንዳለ ሲያሳልፍ ይውላል፡፡  በተመሳሳይ መንገድ ወፈጥ ደንጋዮችም አለቁ፡፡ ጎላ ጎላ ያሉት ደንጋዮችም ተመናመኑ፡፡  ዉኃ ሲያናግራቸዉ ኖረ አሁን ደግሞ መዶሻ ፈጃቸው፡፡ ይህም ሁኔታ ደግሞ ለልዝብ ጠቅሟል፡፡ ልዝብ እያሙለጨለጨ ወደ ዳር በመዉጣት የመጣውን ማእበል ሁሉ በማምለጥ ወዝቶ አምሮበት እያብለጨለጨ ይኖራል፡፡  ወፈጥና ደንጋዮች በነበሩበት ዘመን የእየተጥመለመለ የሚመጣዉን ጎርፍ መከራና ስቃይ ሁሉ በተባ ብእራቸዉ ይከላከሉልን ስለነበር ዉኃ እኛ ጋ ሳይደርስ ኖረ፡፡ ከማናገር የማይቆጠብ ውኃ ዛሬ እነሱን ሲያጣ ስራ ከምፈታ ብሎ እኛ ጠጠሮቹ ጋም ደረሰ፡፡ ንግግሩን ከላይ እንደተጠቀሱት ብእረ-ርቱአን ማቅረብ አልቻልንም እንጅ ይኽው እኛ ጠጠሮችም በዉኃ አስጋዳጅነት መናገር ጀመርን፡፡ በአሁኑ ወቅት ጠጠር ጋ የደረሰ ዉኃ ያላሳዘነው ወይም ያላስለቀሰው የደንጋይ ዘር ካለ፤ ልዝብ ወይ ደለል አለዚያም አፈር ሆኗል ማለት ነውና ታድሏል፡፡

ዛሬ የምግብ መቅመሻ በሌለኝ ሰዓት ከሚያናግሩኝ ዉኃዎች መካክል አንዱ መንገድም ሆነ አገር ብቀይር አላመልጠው ያልኩት፤ ወቅት ያልቀየረው፣ የጷጉሜ ዉኃ ያልሻረው “የወንዙ፣ የጅረቱ፣ የተራራዉ፤ የሜዳዉ፣ የዚህኛዉ፣ የዚያኛው፣ የቅርቡ፣ የሩቁ፣ የቀዩ፤ የቀይዳማው፣ የጠይሙ፣ የጥቁሩ ወዘተ ነፃ አዉጪ” በሚሉ ስሞች ራሱን የሰየመ ዉኃ ነው፡፡ የነፃ አዉጪዎች ከአንድ በላይ መሆን የሚያሳየው ነፃነትን የሚሹት ክፍሎች ብዙ መሆናቸዉን ነው፡፡ ይኽኛዉም ያኛዉም፤ ቀዩም ጠይሙም፤ ሌላዉም ሌላዉም፤ ነፃነትን ይፈልጋሉ ማለት ነዉ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የእዉነትም ይሁኑ የዉሸት የነፃ አዉጪዎች መብዛት አንደኛው ቡድን ለሌላኛው ቡድን ደንታ የሌለው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የጥቁሩ ነፃ አዉጪ ለቀዩም ቢያስብ የቀዩ ነፃ አዉጪ ባልተፈጠረ ነበር፡፡ እንዳዴ እንዲያዉም ጥቁሩ ወይም ቀዩ ራሱ አራትም አምስትም ነፃ አዉጪ ሲኖረዉ ይታያል፡፡ ታዲያ ይህ የሚያናግር ዉኃ አይደለም ጎብዝ? ቀዩ ቡድን የቀይ ቡድን ነፃ አዉጪ ሲያቋቁም፤ ሰለሌላዉ ቡድን ደንታ የለኝም እንደማለት ሊቆጠር ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ይህ የራስን አእምሮ ነፃ ካለማዉጣት የሚመነጭ ነው፡፡ ነፃነት ሁለንተናዊ (ዩኒቨርሳል) ፅንሰ-ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህ መጠቀመም ያለብን ለሁለንተናዊ ጉዳይ ነው፡፡ ለሁሉም የተፈጠረዉን በግድ ለተወሰነ ቡድን ብቻ ልናዉለዉ ብንሞክር ወደ ተፈጥሯዊ ወርዱ ለመዘርጋት ሲታገል ይቀዳደድና ምንነቱን ያጣል፡፡ የነፃነትን ስጋ-ወ-ደሙ የተጎነጬ ሰው ወይም ቡድን ቀለም፣ ዘር፣ ወርድ፣ ስፋት ወዘተ አይለይም፡፡ የሌላውን ነፃነት ማጣት እንደራሱ ቆጥሮ ለሁሉም የተቻለዉን ያደርጋል፡፡ በእዉን የምናየው ግን የተገላቢጦሹን ነዉ፡፡ ቀይዳማና ጠይም ተፋቅረው በሰርግ አብረው ሲጨፍሩ፤ በለቅሶም አብረው ሲያለቅሱ፤ መጠጡን ምግቡን አብረው ሲካልፈሉ፤ ከዚያም አልፎ ልጅህን ለልጄ ሲባባሉ እየታዬ “ነፃ አዉጪ ቡድኖች” ቀይዳማና ጠይሙን አይጥና ድመት አስመስለዉ ያቀርቧቸዋል፡፡ አብሮ መኖር ቀርቶ አንዱ በሄደበት ሌላዉ ክልዉስ ሊል የማይችልበት የተፍጥሮ ግድግዳ ያለ አስመስልዉ ይስላሉ፡፡ በአንድ አምሳል የተፈጠሩትን  በተለያየ መንፈስና ኃይል የተፈጠሩ አስመስለዉ ያዋራሉ፡፡ ታዲያ ይህ ጠጠርን ሳይቀር እግዚኦ አሰኝቶ የሚያናግር  የጎርፍ ማእበል አይደለምን?

ሌላም የጠጠርን ድምፅ ከፍ የሚያደርግ ነገር አለ፡፡ “ነፃ አዉጪ” ብለው ራሳቸዉን በመሰየም የሚንቀሳቀሱት አብዛኞች ቡድኖች እንታገላለን የሚሉት ኢፍትሐዊነትን ሳይሆን ፍትህ የነፈገዉን ቡድን ነው፡፡ የፍትህ ንፍገትን የማይታገል ግለሰብ ወይም ቡድን መቸዉንም ቢሆን ፍትህ ከማጣት አይድንም፡፡ ነፃነት ወይም ፍትህ ማጣት እስካልተወገደ ድረስ ይኽኛውን መብት-ገፋፊ ቢጥል ሌላኛዉ እስተንፋስ-ነሽ በሌላ በኩል ሳይጋበዝ፤ እንደ ድንገተኛ ቆሌ ቤት-ለእንቦሳም ሳይል ዘው ብሎ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ለአበሻ መንገር ደግሞ ምጥ ለእናቷ አሰተማረች ይሆናል፡፡ ኢፍትሐዊትን ችላ ብሎ ከፍትህ ነፋጊዉ ጋር ብቻ ግብግብ መግጠም የወባ ትንንኝ የምትጠፋበትን መንገድ መቀየስ ችላ ብሎ ለትኩሳት ማዳኛ አስፕሪን ፍለጋ ሁሌ አቶ ሙደሲር ሱቅ እንደመሮጥ ይቆጠራል፡፡ ለወባ ትኩሳት ማስታገሻ ስንገዛ ኖረናል፡፡ ወባ ግን እንዲያዉም ከበፊቱ እጅግ በርትቶ ወገናችንን በመደዳ እየፍጀ ዛሬም የኅዘን ድንኳን ሲያስተክለን ይውላል፡፡ የወባ ትንኝን ማጥፋት በወባ የመጣን ትኩሳትን ብቻ ሳይሆን ወባን ራሱ ማጥፋት ነው፡፡ ኢፍትሐዊነትን ማጥፋትም አንድን ፍትህ-ንሽ ቡድን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ይኽንን ርኩስ መንፈስ ከራስም ሆነ ከሌሎች ናላ ጠራርጎ ማዉጣት ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል “ቢ እንድታገኝ ለ ኤ ብለህ ሥራ” የሚባል የፈረንጅ አባባል አለ። አዎ ራስን ለ “ቢ” ዉጤት ብቻ ወስኖ የበለጠ ጥረትን ቢያቆሙ “ሲ”ም አዳልጦ “ኤፍ” ላይ መንጠር ሊመጣ ይችላል፡፡ ለአለም ነፃነት የሚታገል ቡድን ቢያንስ ለአንድ አህጉር ሊበጅ ይችላል፡፡ ለአህጉሩ የሚታገል ቡድን ቢያንስ ለአንድ አገር ይበጃል፡፡ ምናልባትም ላገሩ የሚታገል ቢያንስ ቢያንስ ለተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ሊጠቅም ይችላል፡፡ “ይኽንን ለኛ ትነግራለህ?” አትበሉኝ እንጅ ከዚህ በጫጨ መርህ ላይ የተመሰረተ ቡድን ግን ዉጤቱ ሁሉ ኪሳራ መሆኑ አይቀርም፡፡ በኛም አገር “የማያድግ ጥጃ ከገመዱ ያስታዉቃል” ይባላል፡፡ ገና ሲጠነሰስ በጠባብ መርህ ላይ የተመሰረተ ነገር ጉዞዉ ሁሉ እያነሱ፤ እየጠበቡ መሄድ ነዉ፡፡ የመጥበብ የመጨረሻው መዳረሻ ደግሞ መበጣጠስ ነዉ፡፡ አዎ! የጠበበ ነገር ሁሉ ሸብቦ ይይዝና፤ተዝናንቶ መንቀሳቀስን ይነሳል፡፡ ዉሎ አድሮም መቀመጥ እንደበዛበት አቡጀዲ ሱሪ መቀደዱ አይቀርም፡፡  እኛ ፈለግነዉም አልፈለግነዉም አለም እንደሆነች አንድ እየሆነች መጥታለች፡፡ ዉጥረቱ የሚፈጠርዉ አለም በራሷ ኃይል እያፈረሰች ያለዉን ድንበር እኛ መልሰን መከለል ስንቀጥል ነው፡፡ ከዉጥረቱ ለመዳን ከመጠበብ መስፋትን እንምረጥ፡፡ ነፃ ለማዉጣት ከመነሳታችን በፊት የራሳችንን አምሮ ነፃ እናድርግ፡፡ ነፃ የሆነ አእምሮ ድንበር የለዉም፡፡ ቀዩን ከቀይዳማው አይለይም፡፡ ጥቁርና ጠይሙንም ሰበብ እየፈጠረ አያላትምም፡፡ ትኩረታችንም ኢፍትሐዊዉ ቡድን ላይ ብቻ ሳይሆን ራሱ ኢፍትሐዊነት ምናብ ላይ ይሁን፡፡ ኢፍትሐዊነትን መታገል ፍትህ-ነሽን መፋለም ብቻ ሳይሆን የራስን ናላ ነፃ ማድረግንም ይጠይቃልና፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ጥቅምት ፲፱፻፺፱ ዓ.ም

 

ድንጋይን የሚያናግረው ውኃ ነው!

ክፍል-፪

እርግጥ ነዉ እንደሚባለዉም ድንጋይን የሚያናግረው ሲጓዝ ዉሎ ሲጓዝ የሚያድር ዉኃ ነው፡፡ እኔን ጠጠሩንም ሳይቀር ብቻዬን የሚያስተክዘኝ ይኸዉ ነው፡፡  በክፍል አንድ ለወፍ ላራዊቱ፤ ለሳር ለቅጠሉ፤ ሳይቀር የሚበቃዉን ፍትህ እነደ ጨርቅ በክንድና በስንዝር እየለኩ ጥቢቆ በመስፋት ለተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል እናላብሳለን የሚሉ “ የቀይ፣ የቀይዳማ፣ የጠይም፣ የጥቁር ሕዝብ ወዘተ ነፃ አውጪዎች” ጠጠርን ሳይፈልግ አናግረዋል፡፡ ዛሬ ጠጠርን የሚያስተክዘው ጎርፍ ደግሞ ከቤተ-ክህነት ይነሳል፡፡

ምእመናን ከቤተ-ክህነት የሚመኙትም ሆነ የሚጠብቁት የፅድቅ መገኛ መንገድን፣ ሰብአዊነትን፣ ሰላምን፣ እርቅን፣ የመንፈስ ልዕልና አርያነትን፣ የሥነ-ምግባር ምሳሌነትንና ሌሎችንም አለም ያላትን በጎ ነገሮች ነው፡፡ በለሙያዎች እንደሚሉት ማእበል የሚፈጠረው የተፈጥሮ ሚዛን ሲናጋ ነው፡፡ ከቤተ-ክህነት የሚመነጨው ጎርፍም መንስኤው ካህናት የተሸከሙት መስቀል፣ ቆብ፣ ማእረግ፣ ቃለ-መሐላ፣ አለባበሳቸውና ሌላውም ሌላምዉም ነገር ከግብራቸው ጋር አራባና ቆቦ ሆኖ አልገናኝ ሲል ነው፡፡ ይህ ችግር ስር የሰደደ መሆኑ እየታወቀ ብዙ ሰዉ ጉዳዩን ባደባባይ ሲያነሳ ብዙም አይታይም፡፡ ብሶቱ፣ ቁስሉ፣ ትዝብቱና ጭንቀቱ ግን ከአብዛኛው ምእመናን ፊት ላይ ተንቀልቅሎ ይታያል፡፡ እንኳን ፊትን ማንበብ ለሚያዉቀው ብዙም ለማይችለው ለኔ ቢጤውም ቢሆን ፍንትው ብሎ ይነበባል፡፡

በመሐንዲሶች ወይም በሐኪሞች የሞራልና የሥነ-ምግባር ጉድለት ለመተቸት የግድ መሐንዲስ ወይም ሐኪም መሆን አያስፈልግም፡፡ የቤተ-ክህነትን የሞራል ማሽቆልቆል ለማንሳትም የግድ መሪጌታ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መነኩሴ ወይም ጳጳስ መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ሙያዎች በጥበባዊ (ቴክኒካል) ባህሪያቸው ይለያዩ እንጂ ሞራላዊ ወይም ሥነ-ምግባራዉ ገፅታቸዉ ይመሳሰላል፡፡ የገበሬዉ፣ የመምህሩ፣ የመሐንዲሱ፣ የሾፌሩ፣ የጠበቃዉ፣ የዳኛው፣የሐኪሙ፣ የካህኑ፣ የነጋዴው፣ ወዘተ ሁሉ የሞራል ግዴታ ለሰው ልጅ በጎ ነገር መስራትና ክፉ ነገርን ሁሉ ማስወገድ፤ የሥነ-ምግባር መርሆዉም በሥራ ብቁ ሆኖ መገኘት፣ አለመቅጠፍ፣ በመቅቡጥ አለመደለል፣ ለፍትህ መስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች በተለይም የክርስትና መሪዎች የእየሱስን መንገድ ለራሳቸው ብቻ መከተል፤ የእስልምና መሪዎችም የመሐመድን ፈለግ መከተል ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በዚሁ ረድፍ የማሰልፍ የሙያም ሆነ የቃለ-መሐላ ግዴታ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊትም ሆነ በኋላ እንደዚህ አይነቱን የሃይማኖት ግዴታ እየተወጡ ያለፉ ነቢያትም ሆነ ሐዋሪያት አያሌ ናቸዉ፡፡

ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር(አላህ) መኖር የምናምንም ሆነ የማናምን፤ የክርስትናን እምነት የተቀበልንም ሆነ ያልተቀበልን፤ በሙሴ የነፃነት ተጋድሎና በየሱስ ፍትሐዊነት ብዙ እንከራከራለን ብየ አላስብም፡፡ እነዚህን ሃይማኖት የተመሰረተባቸዉን አለቶች በፈጠራ ታሪክ ተዋናዊነት የሚመድቧቸው “ቁስ-አካላዊ” ነን የሚሉት እንኳን ሙሴና እየሱስ የተናግሩት ወይም የሰሩት ትክክል አልነበረም ሲሉ በበኩሌ ሰምቼ አላዉቅም፡፡ ከአባይ ወንዝ በደንገል ተጠቅሎ በፈርኦን እህት አማካኝነት የተገኘዉ ሙሴ (ሙሴ = ከዉኃ ዉስጥ የውጣ) ዘጸአት ፪፡፲ {1} ያደገዉ በፈርኦን ቤተ-መንግስት ነበር፡፡ ነፍስ እያወቀ ሲመጣ ፈርኦን በእስራኤላዊያን ላይ የሚፈፅመዉን አድሎአዊ ያስተዳደር በደል ሲመለከት የቤተ-መንግስቱን የድሎት ኑሮ እርግፍ አድርጎ ለመተው ወሰነ፡፡ ለፍትሕ ሲል ጉረሮዉን ለጥማት፣ ሆዱን ለርሃብ፣ ቆዳዉን ለርዛት አሳልፎ ሰጠ፡፡ ፈርኦን በባርነት ከሚገዛቸው፣ ከሚገላቸው፣ ከሚገርፋቸውና ከሚያሳድዳቸው የእግዚአብሔር ልጆች ጋር አብሮ ቆመ፡፡ መብል መጠጡ የተትረፈረፈብትን፤ ስጋጃ የተነጠፈበትን አለም ትቶ ምርኩዙን አንጥልጥሎ በበርሃ ተጓዘ፡፡ ሕዝቡንም ወንድ የሆነ ሂብሩ ህፃን ልጅ በመግደል ወይም በማስገደል ከታወቀዉ አረመኔው ፈርኦን መንጋጋ በእግዚአብሔር ፈቃድ አላቀቀ፡፡ {1} ነፃም አወጣቸው፡፡ ሙሴም እንኳን የሰዉን የልብ፤ የመለኮትን መስኮት አስክፍቶ ከእግዚያብሔር በቀጥታ ለመነጋገር ቻለ፡፡ በሰዉ ልጅ ዘንድም ይኸው ከአጥናፍ አጥናፍ በደግ ስራዉ ይነሳል፡፡ አምስቱ መጻሕፍቱ ይነበባሉ፡፡ ብዙ ሰዉም ልጁን በርሱ ስም ይሰይማል፡፡ ይኽንን አስተዉሎ አሁን ባገራችን ያለዉን ሁኔታ ያገናዝቧል፡፡ ከቀርብ ጊዜ ወዲህ ያሉ የኛ የቤተ-ክህነት ሰዎች ያማረ ካባቸውን ደርበው፣ “የተዋበ” ቆባቸዉን ግጥም አርገው የሙሴን መጻሕፍት በመጥቀስ የሚስተካከላቸው የለም፡፡ ነገር ግን እርሱን እንደ አርያ ወስደው እንኳን ነፃ  ሊያውጡን እንደበሬ አፍነው “እኛ ያልነዉን ብቻ ተቀበሉ!” ከሚሉ ገዥዎቻችን ጋር አብረው ያሹናል፡፡ እንደ ገብስ ያፍተለትሉናል፤ እንደላምም ያልቡናል፡፡ እንዲያም ሲል ያሳስሩናል፤ ያይን ብረታቸዉ እያየ ያሰገድሉናልም፡፡ እጃቸዉን ግን ለስለት መይም ላስራት ካስገባነዉ መዋ አያነሱም፡፡ ታዲያ ይህ በድንጋዮች ማለቅ የተጋለጠውን ትንሽ ጠጠር ማናገር ይነሰው?

እንደ ሙሴ ሁሉ በእየሱስ ክርስቶስ አምላክነት የምናምንም ሆነ የማናምን ባስተላለፋቸዉ መልእክቶችና ሰራቸዉ  በተባሉት ሥራዎች በጎነት ክርክር ዉስጥ የምንገባ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ  ሕግን እያነበነቡ ነገር ግን የማይፈጽሙ ፈሪሳዉያን በሌላ  በኩል ደግሞ የሮማዉ ንጉስ አዉግስቶስ ቄሳርን ወክሎ እየሩሳሌምን ያስተዳድር የነበረዉ ሄሮድስ ተሰሚነቱን ስልፈሩት ሁለቱም ወገን ተስማምተዉ በተሸከመው ግንድ ወስደዉ ሰቀሉት፡፡ {2,3}. እርሱ ግን  ወቅቱ ለተመቻቸው ለሁለቱም ወገን ክንዳሞች ሳያጎበድድ ህይወቱን አሳልፎ ሰጠ፡፡ በደሙ የዋጀው እምነትና ስሙ ግን በአለንባት ምድር ከተስፋፋ ይኸው አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ዘመን ተቆጠረ፡፡ ሳይነጋ ሶስቴ እየሱስን የከዳዉ ስምኦን ጴጥሮስ እንኳን እየሱስ ከሞተ በኋላ የበለጠ በእምነቱ ፀንቶ እየወደቀ እየተነሳ የክርስትና እምነትን በሮም አለት ላይ ተከለ፡፡ {6,7} ዳሩ ግን እርሱም በበጎ ስራዉ ምክንያት ተገደለ፡፡ እንዲያዉም እየሱስ ራሱ ወደ ላይ ሆኖ ስለተሰቀለ ከሱ ላለመወዳደር ሲል ራሱን ወደ ታች ዘቅዝቀዉ እንዲገሉት ስለጠየቃቸው ታርዶ እደሚገፈፍ በግ ዘቅዝቀዉን ነው የገደሉት እየተባለ ይነገራል፡፡ {6,8}. ሐዋርያዉ ጳዉሎስም እንደዚሁ ለህዝብ በሰበከዉ እምነትና በበጎ ስራዉ ምክንያት ከአንገቱ ላይ ተቆርጦ ተጣለ፡፡ {6, 8} ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ቅዱስ ጳዉሎስ በሰዉነት የማይቀረዉን ሞት ሞተዋል፡፡ ሰው ባካል ያላዬውን የሰማዩን ጽድቅ እንኳ ብንተወዉ በምድር መጽደቃቸዉን ማየት የሚሳነዉ ያለ አይመስለኝም፡፡ ቤተ-ክርስቲያኑ፣ ሰዉ ፣ ከተማው፣ መንገዱ፣ አንዳድ አካባቢ እንሰሳው ሁሉ ሳይቀር በነሱ ስም ይሰየማል፡፡ ልጁን በይሁዳ ስም የሰየመ ክርስትያን በተለይም ኢትዮጵያዊ እስካሁን አልሰማሁም፡፡ የሚያሳዝነዉ ዛሬ በጎቻቸውን በቀበሮ የሚያስነጥቁ፤ በማጭበርበርና በማታለልም ቆዳቸዉን እየገፈፉ የሚበሉ ልግመኛ እረኞችም በእኒያ እየሰሱስ በመረጣቸው ሐዋርያትና ሰማእታት ስም እየተሰውየሙ ቅዱስ ስማቸዉን ማርከሳቸው ነው፡፡ ምእመናን፣ የስራ ባልደረባ የሆኑት ማተባቸዉን ያልቆረጡ ካህናት በእመነታቸው ምክንያት ብቻ እንኳን ሲሞቱ እንኳን ገዳይን ሊገስፁ ለሞቱት ጸሎት ማድረስም ይከብዳቸዋል፡፡ ከሚያልቀው ህይወት ሁሉ የነሱ ጉርስ፤ የሚተኙበት አልጋ የሚንፈላሰሱበት መኪና ይበልጣል፡፡

እነ ጳዉሎስን የተኩ አቡን እየተባሉ የሚሾሙት ጳጳሳት አስፈላጊነት የእየሱስን ወረድ ብሎም የጴጥሮስ፣ የጳዉሎስንና መሰል ሐዋርያትን ስራ በቀጣይነት ካለማመንታት፤ ስጋቸዉ ሳያሸንፋቸዉ እምነትን እንዲያስፋፉ በጎቻቸዉን እንዲጠብቁ ነበር፡፡ በርግጥም አንዳድ ትጉህ የሆኑ፣ ለመስቅልና ለማተባቸው የተገዙ አልጠፉም፡፡ ወደ ሁኋላ ሄደን ብዙም ሳንርቅ የግብፁን አቡነ ሽኖዳና የእኛዎቹን ሰማእታት አቡነ ጴጥሮስናን አቡነ ቴዎፍሎስን ለእነዚህ ምሳሌዎች ይሆኑናል፡፡

የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን መቶ አስራ ሰባተኛው ጳጳስ የሆኑት አቡነ ሽኖዳ የክርስትናን ሃይማኖት ሕዝባቸዉ በሄደበት ያለም ክፍል በማስፋፋት የታወቁ ብፁእ አባት ናቸው፡፡ ከዚህ አልፎ ክርስቲያኖች ግፍ ሲፈፀምባቸው እኔን መጀመሪያ ግደሉኝ ብለው ከፊት የሚገኙ ለመሆናቸው እንኳን  በጎች ቀበሮዎችም ይመሰክሩላቸዋል፡፡  ለበጎቻቸው ትጉህ እረኛ ሆነው በመቆማቸው እ.ኤ.አ በመስከረም 1981 አንዋር ሳዳት ከቦታቸው አባረራቸው፡፡ {8} አቡነ ሽኖዳ በጎቻቸዉን ለቀበሮ በመገበር ድሎታቸዉን ለመጠበቅ በመቅቡጥ አልተደለሉም፡፡ ለሳዳት ክርንም አላጎበደዱም፡፡ በጎቼን ቀበሮና ተኩላ ሲበላቸው ከማይ እኔኑ የግብፅ በርሃ አቃጥሎ ይግደለኝ ብለው ወደ በርሃ መነኑ፡፡ ለስጋቸዉ ቢሳሱ ኖሮ ምድራዊ አለቃቸዉ ያላቸዉን ተቀብለው ጥይት እማይበሳው መኪና እየነዱ፣ አባቱ ነኝ ከሚሉት ምእመናን እየተደበቁ፤ በጠበደሉ ወታደሮች እየተጠበቁ  እልፍኝና አዳራሽ እየቀያየሩ፤ እንደ ሕጻን ልጅ ጉንጭ ትምክ ከሚል ፍራሽ ላይ እየተንፏለሉ መኖር በቻሉ ነበር፡፡ ሌላው ከሰማእታት የሚያመሳስላቸው ደግሞ  የተሰደዱት ዋሽንግተን ዲሲ ወይም ለንደን አለመሆኑ ነው፡፡ ምግም ሆነ ዉሀ ከማይግኝበት እንደሳት ከሚያነድ አሸዋማ የግብፅ በርሃ ዉስጥ አምላካቸዉን ተማምነው ሄዱ፤ ነጎዱ፡፡ {8} አዎ አብርሃምም፣ ሙሴም፣ እየሱስም ከናቱ ጋር የተሰደዱት ወደ በርሃ ነበር፡፡ ያባረራቸዉ አንዋር ሳድት ዛሬ የለም፡፡ እርሳቸዉ ግን ዛሬም የኢትዮጵያን ቤተ-ክርስትያን አንድ አስራኛ የሚሆን አባል የሌላትን የግብፅ ቤተ-ክርስትያን እንደቀደምቶቻቸው ሁሉ ባለም ትልቅ መድረክ ላይ ተክለዋት ይገኛሉ፡፡ ይኽዉ እንደኔ አይነቱንም እየማረኩ እንዲፅፍላቸዉ ያደርጋሉ፡፡ ስማቸዉም እንደ ሐዋርያዉ ጴጥሮስ ሁሉ ባለት ላይ ተፅፏል፡፡ እስከ ዘላለምም ይነበባል፡፡ ይህ በጎ ሥራቸዉ እስካለም መጨረሻ እንደሚነሳ ጥርጥር የለኝም፡፡ ታዲያ ይኽንን አዉቆ አሁን በተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ያለውን የሞራል ቀውስ ያስተዋለ ጠጠር እንዴት አይዘን? ነገ ለምንተወው ምድራዊ አለም ካህን የነፍስ ልጁን ለተኩላ ገፀ-በረከት ማቅረቡን የተገነዘበ ጫጩት ድንጋይ ምነው አይናገር?

ጥቁሩ ቆዳቸዉ ሸፍኗቸው የስራቸዉን ያህል ስማቸው ባለም ላይ አልዋለም እንጅ ፋጣሪ ምስጋና ይግባዉና እኛም   ሐዋርያትና ሰማእታት ነበሩን፡፡ አካለቸው ቢለየን መንፈሳቸው ዛሬም አብሮን ነዉ፡፡ ምናልባት መኖራቸዉ አልታወቅ  ብሎ እንጅ ዛሬም በየገዳማቱ በጸሎት የሚማፀኑልን አባቶች አሉን ብየም አስባለሁ፡፡ አገራችን በግፈኛው መሶሎኒ በተወረረችበት ወቅት እንደሙሴ ዘንጋቸዉን ይዘዉ ነፃ ሊያወጡን የተነሱ እቡነ ጴጥሮስ የሚባሉ የበቁ አባት ነበሩን፡፡ ሙሴ የፈርኦንን እብሪት ከምንም እንዳልቆጠረው ሁሉ አባታችን ጴጥሮስም የመሰሎኒኒ ባለሟሎች ዛቻ ከቁብ ሳይቆጥሩ ለሕዝባቸው ባደባባይ ጸለዩ፤ ታገሉ፡፡ ፋሽሽት አርፈው እንዲቀመጡ አለበለዚያ ሊገላቸውም እንደሚችል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸዉም “የአገሬን ሕዝብ በመርዝ ጋዝና በቦንብ ስትፈጀዉ የሚያሰማው ጩኸት ሀሌናየን እንዴት ብሎ እረፍት ይሰጠዋል?” ብለው ከኢሳያስ መጽሐፍ የሚከተለዉን ጠቀሱ፡፡ ኢስ ፶፩፡ ፯ “ጽድቅን የምታዉቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብም ሆይ ስሙኝ፤ የሰዉ ተግዳሮት አትፍሩ፤ በስድባቸዉም አትደንግጡ፡፡ እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፡፡ እንደበግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል፡፡ ጽድቁ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትዉልድ ሁሉ ይሆናል፡፡”  {8} አዎ እርሳቸው እንዳሉት ፋሽሽትን ትልም ብልም በላዉ፡፡ በእንደነሳቸው አይነት አባቶቻችን መሰዋእትነት ይኽው የነሱ ትዉልድ እኔን ጨምሮ ከቅኝ አገዛዝ መከራ ድነናል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ በመላዉ አለም በችግር፣ በርሃብና በበሽታ በምንታወቅበት ዘመን እንኳን ደረታችንን እንደ ጭድ ክምር ወደ ላይ እየነፋን “ማን ከኔ ተስተካክሎ” በሚል መንፈስ እጃችንን በኪሳችን እየከተትን እንጀነናለን፡፡ ግዳይ እንደጣለ ጀግና እንጎማለላለን፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የብፁኡ የአቡነ ጴጥሮስና የመሰሎቻቸዉ መንፈስ ሳይሆን ይቀራል?  ሰማእቱ አባታችን የሚወዷትን አገራቸዉና የነፍስ ልጅ የሆነዉን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጨረሻ ጊዜ በአረመኔው ፋሽሽት የቅስፈት ሐይል ሲለዩም “ የፋሽስቱን የወረራ ሐይል እንዲመልስ እግዚያብሔር ሆይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታቱንና ጥንካሬዉን ስጠው!” ብለው መስቅላቸዉን ባራቱም አቅጣጫ አማትበዉ ጸለዩ፡፡ በመቀጠልም “ የኢትዮጵያ ምድርም ለፋሽሽት አትገዛ” ብለው ገዘቱ፡፡ {7,9} እግዚያብሔር ጸሎታቸውን ሰማ፤ የሕዝቡን ክንድ ከዳር እስከዳር አበረታላቸው፡፡ አጠነጠነው፡፡ ፋሽሽትንም መግቢያ መድረሻ አሳጣው፡፡ ደቆሰው፡፡ ምድሩም የተባለውን አደረገ፡፡ ተራራው፤ ጫካዉ፤ ዳገቱ፤ ቁልቁለቱ ከፋኖው ተወዳጀ፡፡ ለፍትህ ታጋዩ እንደጋሻ ሆነ፡፡ ወንዞችና ሐይቆች ጀግኖችን አጠጡ፡፡ ፋሽሽትና ባንዳዉን ደግሞ ዋጡ፡፡ አሰመጡ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ያሉት ሁሉ ሆነ፡፡ አበሻ ነፃነቱን ጠበቀ፡፡ ምድሩም ለፋሽሽት ሳይገዛ ቀረ፡፡  በጴጥሮስ ዘንድ ቃል እዉን ሆነ፡፡  በኛ ዉስጥም ሰረፀ፡፡ የጴጥሮስ ቃል ገና በልጅ ልጅ ልጆቻችንም ሲሰርፅ ይኖራል፡፡ አዎ! ይኖራል፤ ይኖራል …

በተመሳሳይ መንገድ በእውቀታቸው፣ በበዙ ቋንቋ ችሎታቸው፣ በሃይማኖት አባትነታቸውና በትእግስታቸው አያሌ ቋሚ ምስክሮች የሚመሰክሩላቸው አቡነ ቴዎፍሎስ በባእድ ሳይሆን አብረዋቸው በሚጸልዩና በሚያገለግሉ “የቤተ-ክህነት” ሰዎችና ሌሎችም ተንኮለኞች አነሳሽነት አገር በቀል በሆነ ፋሽሽት ተገለዋል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ ለወቅቱ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም በጣም አርቆ አሳቢ ስለነበሩ ይህ የዛሬው ጉዳይ እንደሚመጣ ታይቷቸው ቤተ- ክርስቲያኑዋ ከሲሶ መሬት ተላቃ በራሷ እንድትተዳደር ለማድረግ ያለደረጉት ጥረት እንዳልነበረ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ የቤተ-ክህነትን ትምህርት ጥራት ለመጠበቅና ከዘመኑ ጥብብ ጋር ለማዛመድም ብዙ ትግል እንዳደርጉ ይወሳል፡፡ ቤተክርስትያኗን ባለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረጋቸውም ጥርጥር የለዉም፡፡ {7} እንዲያዉም ሌሎች እህቶች የሆኑ ቤተክርስትያናት እስካሁን ድረስ በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አባትነት በፀሎት ጊዜ የሚያስታዉሷቸው እርሳቸውን ነው ይባላል፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስን  እንደፈለገው ሊያሽከረክረቸው ያልቻለው፤ የአምላክን መኖር የካደ አገር በቀል አጥፊ እርሳቸውንም እንደ ጴጥሮስ ቀጫቸው፡፡ እንደዛሬዎቹ አንዳንድ ጳጳሳት ገዳዮች ሲዘፍኑ አብረው ለመዝፈን ፈቃደኛ ቢሆኑ ኖሮ በእስር ቤት ተንገላተው፣ እግር ተወርች ታስረው ባልተገደሉ ነበር፡፡ በሰዉነታቸው ሊያመልጡት የማይችሉትን የስጋ ሞት በሌላ ሰው እጅ አጥተዋል፡፡ ስማቸው ግን እንደ ሐዋርያዉ ጴጥሮስ ሁሉ ባለት ላይ ተቀርሷል፡፡ ሲነበብም ይኖራል፡፡

እንግዲህ ያለፉትን ሰማእታት አነሳሳን፡፡ የሙሴንና የእየሱስን ስቃይና መከራ፣ የሐዋርያቱን ጳውሎስና ጴጥሮስን እሟሟት፤ የሽኖዳን ትግል፣ የሰማእታቱን ጴጥሮሰ- ዘኢቶጵያና አቡነ-ቴዎፍሎስን ታጋድሎና ሞት በማንኪያ ጨልፈንም ቢሆን አዋሳን፡፡ ይኸንን ላፍታም ቢሆን ከቃኘን በኋላ እንደኔ ከሆናችሁ በአእምሯችሁ የሚጉላላው “ዛሬስ ማን አለን ነው?” በአሁኑ ሰዓት እንደጴጥሮስ ለፋሽሽቶች እንዳይገዛ የኢትዮጵያን ሕዝብ ክንድ አጠንክር ብሎ የሚፀልይ አባት አለን ወይ ነው? መልስ ካላችሁ ንገሩኝ፡፡ እኔ እንደሁ ላመታት ይኽንን ጥያቄ ራሴን ደጋግሜ ጠይቄ ያገኘሁት መልስ “ጽድቁ ቀረቶ ባግባቡ በኮነነኝ” የሚል ነው፡፡ ብዙዎቻችሁም መልስ አጥታችሁ በሆደ ባሻነት፤ በትካዜና በምሬት መሬት የምትጭሩ ይመስለኛል፡፡ በዚች ወቅት እንኳን ለዘመናት በፍቅር አብረው የኖሩ ወገኖቻችን ባለማወቅ በሃይማኖት ሰበብ እርስ በርሳቸው በመተላለቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሃይማኖት አባት ነን የሚሉት ግን ሟቾቹ ባስገቡት የአስራትና ስለት ገንዘብ በተገዛ፤ ቆንጨራም ሆነ ጥይት በማይበሰው ዙፋን ያለው አዉቶሞቢል ዉስጥ ተቀምጠው በመንፈስ-ቅዱስ ሳይሆን እንደ ኮርማ በሚቀለቡ ወታደሮች እየተጠበቁ ይኖራሉ፡፡ ይህ የማያሳዝነው፣ የማያስተክዘውና የማያስቆዝመው ካለ ታድሏል፡፡

እንደ ጥንቱ እንደ ጥኋቱ ከቤተ-ክርስቲያን መሪዎች እጅ ፀበል መፍሰስ ሲገባው ዛሬ ግን በጳጉሜና በጥምቀት ሳይቀር የጎሸ ውኃ ይንፏፏል፡፡ እንኳን ከነፍስ አባት እጅ ከምድር የሚፈልቅ የጎሸ ዉኃም ለሰው ልጅ ጠንቅ ነው፡፡ እኛ እንደሁ ሞኞች ነን፡፡ የቤተ-ክርስትያን መሪዎች የነፈጉንን ምህረት ነፍጥ ያነገበ ገዥ ባለመስጠቱ እንወቅሰዋለን፡፡ መስቀልን የጨበጡ፣ ቆብን ያጠለቁ ከእዉነት ሲለያዩ እነ ሕይወት-ኳሱን ቀጠፉ ብለን እናማቸዋለን፡፡ አቡንና ጳጳስ ለማይመጥኑት ወንበር ሲሽቀዳደሙ እያየን ሌሎች የማይገባቸዉን ወንበር በመንጋጋቸው ነግንገው ያዙ ብለን ቆሽታችን ድብን ይላል፡፡ “ያሳ ግማቱ ካናቱ” ይላል ተረት የማያልቅበት ያገሬ ሰው፡፡ ችግራችን ከላይ ነው፡፡ አዎ ከላይ! ከላይ አላግባብ ከተሰቀለው “ቆብ”! እንደ ጴጥሮስ አይነት ቃልን ከስጋቸው ያዋሃዱ ሁለት ሶስት የሃይማኖት አባቶች ቢኖሩን የንፁሐን ደም ጠብ ሳይል ችግራችን በጊዜ በተፈታ ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ጴጥሮስም ሆኑ ቴዎፍሎስ ተመልሰው  መጥተው ውኃን ገና አልባረኩም፡፡ ውኃዉም ገና ጸበል አልሆነም፡፡ እኛም ገና አልተጠመቅንም፡፡ ሐጥያታችንም ገና አልጸዳም፡፡ በሥጋም ሆነ በነፍስ ለመዳን የየሱስን ፈለግ በመከተል ለበጎቻቸው ልእልና ሲሉ የመከራን ጽዋ የጠጡትን፣ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የጴጥሮስንና የቴዎፍሎስን አይነት ትጉሐን እረኞች ተርበናል፡፡ ከእጃቸው ድፍርስ ውኃ ሳይሆን ጸበል የሚያፈልቁ የነፍስ አባቶችን  ተጠምተናል፡፡  ርሃቡን ያስታግስልን፡፡ ጥማታችንን ይቁረጥልን! አሜን፡፡

ዋቢ

  1. ኦሪት ዘጸአት

  2. የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፫

  3. የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፱

  4. የሐዋርያው የጴጥሮስ መልእክት

  5. የሐዋርያው ጳዉሎስ መልእክቶች

  6. ነገር ሃይማኖትና ሥልጣነ መንግስት በሮማ ግዛት (ዳዊት ብርሃኑ)

  7. ጴጥሮስ በዚያች ሰዓት (ሎሬት ጸጋዬ ገብረ-መድህን)

  8. The free encyclopedia

  9. Fesseha Mekuria and SVen Rubenson: A Short life history of martyr bishop Abune Petros who became martyr on the 29thof July 1936, in Addis Ababa Ethiopia in the struggle against colonialism and oppression. 

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

Abbay media.com

Advertisements

Posted on December 8, 2012, in News, Politics. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s