ሰላማዊ አመፅ ማካሄጃ መንገዶች

1. የሰላማዊ ኣመጽ ብያኔ
በቀላል ኣገላልጽ ሰላማዊ ኣመጽ ማለት ከ ኣክብሮት ጋር ኣንስማማም ማለት ነው። ይህም በመሆኑ ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ በምንም መለኪያ ከሽብርተኝነት ጋር ሊያያዝ ኣይችልም። ሰላማዊ ኣመጽ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውንና የማይፈልገውን በግልጽ የሚያሳይበት ኣውድ ነው።
2. እውን ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ሊሰራ ይችላልን?
የሰላማዊ ኣመጽን ታሪካዊ ኣመጣጥ ስናይ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ490 ኣካባቢ በ ሮም እንደተጀመረ ኣዋቂዎች ይናገራሉ። ይህ የትግል ስልት ዘዴው እያደገ መጥቶ የቅርብ ጊዜ የኣለማችንን ታሪክ እኳን ስናይ ከ 1996 ጀምሮ እስከ 1999 የተለያዩ ሃገራት ህዝቦች በዚህ የትግል ስልት ተጠቅመው ከኣምባገነን ስርኣቶች ለመላቀቅ ባደረጉት ትግል ከስልሳ ሰባቱ ሃምሳ የሚሆኑት ኣመርቂ ውጤት እዳስመዘገቡ እናነባለን።

ኣንዳንድ ወገኖች ሰላማዊ ኣመጽን ለማካሄድ ከመነሻው ትንሽም ቢሆን የፖለቲካ ክፍተት (political space) ሊኖር ይገባል፣ ትንሽም ቢሆን ህጋዊ ከለላ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ይህ መረዳት ከሰላማዊ ትግል ጋር ተደባልቆ የመጣ ሳይሆን ኣይቀርም።እውነት ነው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ትንሽ የፖለቲካ ምህዳር ያስፈልጋል። ሰላማዊ ኣመጽ ግን ከሰላማዊ ትግል የሚለይ ሲሆን በየትኛውም መንግስታት ይሰራል። በ ኦቶክራቶች፣ በኮሚኒስቶች፣ በዴሞክራቶች፣ በነገስታት በሁሉም ሁኔታ ይሰራል።

የኣጭር ጊዜ የኣለማችንን ታሪክ ስናይ በሰርቢያ በ 1998 (Otpor!) (ተቃውሞ) የተሰኘው የወጣቶች ሰላማዊ ኣመጽ ኣምባገነኑንና በቦስኒያ፣ ክሮሺያ እና ኮሶቮ በፈጸመው የጦር ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ በፈጸመው (Crime against humanity) ወንጀል ተጠያቂ የሆነውን ስሎቮዳን ሚሎሶቪክን ከስልጣን ለማውረድ የቻለ የትግል ስልት ነው። በሶቪየት ህብረት ጊዜ የተነሱ የነጻነት ጥያቄዎች ውስጥ ይህ የትግል ስልት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በፖላንድ፣ በፊሊፒንስ፣ በሃንጋሪ፣ በቼኮዝሎቫኪያ፣ በቡልጋሪያ፣ በቺሊ ወዘተ. ተፈትኖ የወጣለት የትግል ስልት ነው።
ይህ የትግል ስልት በኢትዮጵያ የማይሰራበት ምንም ምክንያት የለም። ሰላምዊ ትግል በኢትዮጵያ ኣስቸጋሪ ወይም የማይቻል ብለው የሚያምኑ ወገኖች ሁሉ በሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ለውጥ ኣይመጣም ማለታቸው ኣይደለም።

የኢትዮጵያ መንግስት ተፈጥሮና የፖለቲካው ኣጠቃላይ ከባቢም ቢሆን ይህን የትግል ስልት እንዳይነሳ የሚያደርገው ኣይደለም።

3. ኢትዮጵያ ለሰላማዊ ኣመጽ የተዘጋጀች ኣገር ናት ወይ?
በኣጠቃላይ ህብረተሰብን ወደ ኣብዩትና ወደ ለውጥ ከሚገፉት ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፣
1. የድህነት መጨመር
2. ኢፍትሃዊነት ፣ ሰፊ የ ኦፖርቹኒቲ እጦት፣ ስራ ኣጥነት፣ ኣድልዎ ወዘተ.
3. ከፍተኛ የገቢ ኣለመመጣጠን (Large socio-economic disparities)
4. የህዝቦች ሉኣላዊነት መደፈር
5. የኣንድነት መደፈርና
6. የብሄራዊ ማንነት መነካት
7. የነጻነት እጦት
እነዚህ ከፍ ሲል የዘረዘርናቸውን ጉዳዮች ስናይ ኢትዮጵያ በነዚህ በሁሉም ጎኗ ቆስሏል። ኣልፎ ተርፎ የነዚህ ችግሮች ጡዘትም በዜጎች ልብ ውስጥ ተፈጥሮኣዊ የለውጥ ጥያቄን ኣብስሏል። ይሁን እንጂ ለሁሉም ጊዜ ኣለው ታዲያ። በለስ ኣብቦ ያፈራና ሲበስል መቆረጥ ኣለበት። ጊዜው ሲያልፍ ጥቅም ኣይሰጥም። የህዝቦች የለውጥ ፍላጎት በከረረበት ሰኣት የሚነሳ ሰላማዊ ኣመጽ ውጤታማ ሲሆን እንዲሁ በየግለሰቡ ቤት እየተብሰለሰለ የሚያደራጀው ኣጥቶ ጊዜ ሲወስድ መጠውለግ፣ መደንዘዝ ያመጣል። ወይም ቁጣው ባልታቀደ መልኩ ይፈነዳና ሊባክን ይችላል። ለዚህ ታዲያ ሃላፊነት የወሰዱ ሃይሎች ወቅቱንና የህዝቡን ብሶት ደረጃ እያዩ ማደራጀት ለሰላማዊ ኣመጽ ማነሳሳትና መምራት ይጠበቃል።

4. በሰላማዊ ኣመጽ የሚመጣ ለውጥ ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ
1. ድሉ የራሱ የህዝቡ ስለሚሆን ውጤቱንም በንቃት ይከታተላል፣ይጠብቃል
ህዝቡ በንቃት የተሳተፈበት ለውጥ ሁልጊዜም የሚኮራበት የሚደሰትበት ስለሚሆን በዚህ መንገድ የሚመጣ ለውጥ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
2. ከሁሉም በላይ ለውጡን ከጥላቻ የጸዳ ስለሚያደርገው ከምንፈራው የ ክብ (vicious) በጥላቻ የተሞላ ትግል ወይም ጦርነት እንድንወጣ ኣዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።
3. ጸጋ ለመግለጥ
የተለያየ ጸጋ ኣለን። ኣንዳንዱ ጥሩ ኣስተባባሪ ነው። ኣንዳንዱ ጥሩ መሪ ነው እነዚህ ጸጋዎች የሚገለጹበት ኣንዱ ኣውድ ይህ ህዝባዊ ኣመጽ ነው። ኣመጹ ሲነሳ ውስጣቸው ያለው ጸጋ እየገፋፋቸው ሃላፊነት እየወሰዱ የሚያስተባብሩ፣ የሚመሩ ሰዎች በዚያው ኣጋጣሚ ተስበው ቀጣዩን ለውጥ የሚመሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙ ታላላቅ መሪዎች በዚህ መንገድ ተፈጥረዋል። እውቁ የፍትህና የነጻነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግ ኣመጽ የወለደው ነው።
4. ህብረትን ለማደስ
ሌላው ከህዝባዊ ኣመጹ ጋር ኣብሮ የሚገለጠው ነገር። ህብረትን ማደስ ኣንድነትን ማጠናከር ነው። የዜጎች ብሄራዊ ስሜት የሚበረታታበት፣ ፍቅርና መተሳሰብ የሚገለጥበት ኣውድ ነው።
5. ሰላማዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ምን መልክ ሊኖረው ይገባል? ማንስ ይምራው? ህዝብ ወይስ የፖለቲካ መሪዎች?
በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ ኣመጽ በሁለት መንገድ የመነሳት እድል ኣለው ብለን እናስብ። ኣንደኛው የታቀደ በድርጅት የሚመራ ሲሆን ሁለተኛው ያልታቀደ በራሱ በህዝቡ የሚመራ። ከኢትዮጵያ ኣጠቃላይ የፖለቲካ ከባቢና ከተፈጠረው ስነ-ልቦናዊና መልካምድራዊ ክፍተት የተነሳ የታቀደው ቢሆን ሳይሻል ኣይቀርም። ያልታቀደ በህዝቡ የሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ሁኔታ ሲታይ በዛ ያሉ እክሎች ያሉበት ይመስላል። ከነዚህም መሃል፣

1. ኣመጹ በራሱ ከተቀሰቀሰ በሁዋላ የግድ የሆነ ቦታ ላይ ኣመራር መፈለጉ ኣይቀርም ታዲያ በዚህ ጊዜ ተዘልለው ያሉም ይሁን ኣገር ቤት ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ምን ያህል ህብረት ኣላቸው? ምን ያህል በኣመጹ ጊዜም ቢሆን ህብረት ፈጥሮ ኣመራር ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ያመጣል። ድንገት የሚፈነዳው የህዝብ ኣመጽ ኣመራር ሲፈልግ ከተለያዩ ኣካላት የተለያየ ኣመራር እየመጣ ግራ ማጋባት ያመጣስ ይሆን? ኣንዳንዶች ህዝቡ ኣብዩቱን ሲያቀጣጥለው ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ወደ ኣንድነት ይሳባሉ የሚል ኣሳብ ይኖራቸው ይሆናል። በርግጥ ይህ ኣይነቱ ተግባር በሰሜን ኣፍሪካው ኣብዮት ታይቷል። ነገር ግን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኣሰላለፍ ስናይ ከሰሜን ኣፍሪካው ስለሚለይ ይህ ኣሳብ ላያዋጣ ይችላል። ቀድሞ ህብረት መፍጠር በኢትዮጵያ ሁኔታ ኣዋጭ ነው።

2. ከፍ ሲል እንዳልነው ባለፉት ኣመታት ከተፈጠረው የስነ ልቦና ክፍተት የተነሳ ኣንድ ቦታ ሳይታቀድ ቦግ ያለ ሰላማዊ ኣመጽ ሌላው የሃገሪቱ ክፍል ለመዛመት ምን ያህል እድል ኣለው? ጎጃም የተነሳ ኣመጽ ናዝሬት ሊያስተጋባ ይገባዋል። ቡታጅራ የተነሳ ኣመጽ ጋምቤላ ኣሶሳ ሊያስተጋባ ሊቀበለው ይገባል። ይህ ካልሆነ በየጊዜው ኣንድ ኣካባቢ ቦግ የሚለው ኣመጽ መንግስት እንዲቆጣጠረው ፋታ ይሰጠዋል። ችግሩንም በቀላሉ ለመቋቋም ያስችለዋል።
እንግዲህ ከነዚህ ጉዳዩች ኣንጻር ስናይ ነው በእቅድ የሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ማካሄድ ሳይሻል ኣይቀርም የሚያሰኘን ።

6. የታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ ለመፍጠር ምን ያሻል?
የታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ ለማነሳሳት የመጀመሪያው ተግባር የሃገሪቱን መልክና ተፈጥሮ የያዘ ህብረትና ኣመራር ነው መሰረቱ። ታዲያ ይህ ኣመራር በነሲብ በህብረት ስም በሩን ቡርቅቅ ኣርጎ መክፈት የለበትም። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ትግል የጎዳው ኣፍጠው የመጡ የመንግስት ደጋፊዎች ትግል ኣይደለም። በራሱ በመንግስት እጅ እየተደራጁ ትግሉን የሚያዳሙ (hijack) የሚያደርጉ ሃይሎች ናቸው። እውነተኛዎቹ ተቃዋሚዎች ደጋፊ እናጣለን በሚል ስጋት ሆዳቸው እያወቀ ዝም ማለት የለባቸውም። ከ እውነት ጋር ሲቆሙ የሚገርመው ህዝብ ኣሽትቶ ያውቀዋል።
በሃገራችን የገና ጨዋታ ጊዜ “ሚናህን ለይ” የሚባል ነገር ኣለ። ሚና ያለዩበት የገና ጨዋታ እሩሯ የትም ኣትሄድም። እንዲሁ ሚናቸው ባለየላቸው ተጨዋቾች ተከባ ትቆያለች።

በቅንጅት ጊዜ በሚያዝያ ወር የታየው ታላቅ ትእይንት ተፈጥሮው ወደ ህዝባዊ ኣመጽ ያደላ ነበር። መንግስት ላፉ ፈቅጃለሁ ቢልም ትራንስፖርት በማሳጣት፣ በካድሬዎቹ ኣማካኝነት በማዋከብ ሰራተኛውን በማስፈራራት ሰልፉን መበተን ፈልጎ ነበር። ህዝቡ ግን ከኮልፌ ቀራንዩ ድረስ በእግሩ መጥቶ ሰልፉን ኣካሂዷል። በቅንጀት ህብረት ላይ ልቡ ስላረፈ፣ በመሪዎቹ ላይ እምነት ስላደረበት ኣውርድ የሚባለውን ለማውረድ ስቀል የሚባለውን ለመስቀል ዝግጁ ነበር። ይህ የሚያሳየው ህብረትና የሚያምነው ድርጀት ካገኘ ህዝቡ በእቅድ ለሚመራ ህዝባዊ ኣመጽ ወደሗላ የሚል ኣለመሆኑን ነው።

7. የሰላማዊ ኣመጹ ሲታቀድ ከግንዛቤ ሊገቡ የሚገባቸው ጉዳዮች

1. ህዝቡን በኣቅሙ የማታግል ስልት
በኢትዮጵያ ሰላማዊ ኣመጽ ቀጣይነት ኖሮት ፣ ለውጥ ለማምጣት እንዲችል የህዝቡን ኣጠቃላይ ኣቅም ያገናዘበ መሆን ኣለበት። በመሆኑም ኣመጹ ሲታቀድ የህዝቡን ንቃተ ህሊና፣ ኢኮኖሚ ሃይማኖትና ባህል ማገናዘብ መልካም ነው። ኣንድ ጊዜ የኣመጽ ኣይነቶችን ሁሉ ቢያሸክሙት የተሰጠውን የቤት ስራ እስከ መጨረሻ ላይወጣ ይችላል። ከሁሉም በላይ ቦግ እልም እያለ ሩቅ ኣይሄድም። በየቀኑ ሰኳር የሚገዛን ህዝብ፣ በየቀኑ ጨው የሚገዛን ህዝብ፣ በየቀኑ ዘይት እየገዛ የየቀን ኑሮውን ለመግፋት የሚታገልን ህዝብ ያየ የትግል ስልት ብዙ ብዙ ኣለ።

2. መቼት (setting)
የታቀደ ሰላማዊ ኣመጽ ሚስጥር ኣይደለም። ለሚሊዩን ህዝብ ተነግሮ ከመንግስት የሚደበቅ ነገር የለም። መቼና የት? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ሊኖረው ይገባል። ለኣብነት የምስራቅ ጀርመኖችን ታሪክ እናንሳ። በ1989 ምስራቅ ጀርመናዊያን ኣምባገነንነትን ለመቃወም ሲያቅዱ
“የሰኞ ኣብዮት” ብለው ተነሱ። በየሳምንቱ ምሽት ላይ በከተማይቱ መስቀል ኣደኣባይ እየተገናኙ ለኣንድ ኣመት ያህል የዘለቀ ተቃውሞኣቸውን ኣድርገዋል። በዚያን ጊዜ ጀርመናዊያን ሰኞን በናፍቆት እየጠበቁ ምን ላድርግ እያሉ እያሰቡ ይቃወሙ ነበር። እያደር ደጋፊያቸው እየበዛ ትግላቸው እያበበ ሄዶ በመጨረሻ የበርሊንን ግንብ ሳይቀር ለማፍረስ እና ለሁለቱ ጀርመኖች ውህደት በር ከፈተ። እቅዳቸው ኣቅማቸውን ጊዚያቸውን ያገናዘበ በመሆኑ ርቀት ተጉዘው ኣሸነፉ።
በኢትዮጵያ የሚነሳ ህዝባዊ ኣመጽም እንዲህ መቼት ሊበጅለት ይገባል። መቼቱ ክርጀርመናውያን የተለየ ሊሆን ይችላል ግን ኣሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ ሁኔታ መቼት መፍጠር ይቻላል።

3. ስያሜ
ህዝባዊ ሰላማዊ ኣመጽ መሪ ቃል ወይም ስያሜ ያሻዋል። በ1986 የኣለምን ቀንደና ሙሰኛ የሆነውን ፈርዲናንድ ማርቆስን የፊኒፒንስ ህዝብ የጣለው የህዝብ ሃይል ኣብዮት “people power revolution” የሚል የትግል ስም ሰይመው ነው። ፊሊፒኖዎች መሪቃላቸውን ይዘው በየጎዳናው በጸሎትና በመዝመር ተቃውመው ማርቆስን ጥለዋል። በባልቲክ ግዛት በላቲቪያ ኤስቶኒያ የመዝሙር ኣብዮት “singing revolution” በሚል ስያሜ በዝማሬ ያለ ምንም ደም መፍሰስ የፈለጉትን ለውጥ ተቀዳጅተዋ።
በዚሁ በክፍለ ኣህጉራችን በ 2003 የላይቤሪያ ሴቶች በጸሎትና በመዝሙር ያደረጉት ተከታታይ ተቃውሞ የላይቤሪያውያንን የርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ችሏል። በሊባኖስ “የዝግባ ኣብዩት”፣ በዩክሬን “የ ብርቱካን ኣብዮት” በጆርጂያ “የጽጌረዳ ኣብዮት” ይጠቀሳሉ። በኢትዮጵያም ቀስቃሽና ነሻጭ የሆነ ስያሜ ቢሰጠው ለትግሉ ሃይል ይሆናል።

4. ትግሉ ሲጦዝ (Climax) ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ከግንዛቤ ኣስገብቶ የታክቲክ ኣማራጮችን ቀድሞ ማስቀመጥ

በኣንድ በተመረጠ መቼትና መሪ ቃል የሚጀመር ህዝባዊ ኣመጽ በኢትዮጵያ ውስጥ መልኩን ሳይቀይር እስከመጨረሻ ላይጓዝ ይችላል።ኣመጹ እየበረታ ሲሄድ ደጋፊዎች ሲበዙ በመንግስት በኩል ሪኣክሽን መፈጠሩ ኣይቀርም። በዚህ ጊዜም ትግሉ ኣቅጣጫውን ሊቀይር ስለሚችል ሊሆኑ የሚችሉትን ውጤቶች በመተመን ኣማራጭ ታክቲክ ቀድሞ ማሰብ የእቅዱ ኣካል ነው። በኣጠቃላይ እቅዱ ያሉትን ፍራቻዎች (threats) ና መውጫቸውን ማስቀመጥ ኣለበት።

5. መረጃ መቀባበያ ዘዴዎችን መፍጠር
መንግስት ህዝባዊ ኣመጽ ብቅ ሲል የመጀመሪያው ሩጫው የመረጃ መቀባበያ ዘዴዎችን መምታት ነው። ይህ እንደሚሆን ስለሚታወቅም መንግስት ሊቆጣጠራቸው የማይችሉ የመረጃ መቀባበያ መንገዶችን መፍጠር ያስፈልጋል። በተለይ በገጠሩ ኣካባቢ ያለው ህዝብ ኣሰፋፈሩ የተራራቀ ስለሆነ ለመረጃ የራሱን ባህል የተከተለ ዘዴ መፍጠር ተገቢ ነው። ለኣብነት ያህል በደቡቡ ያገራችን ክፍል ኣንድ ቀበሌ ህዝብ ሲያምጽ ወይም ችግር ሲደርስበት ከፍታ ቦታ ላይ ጭስ ያጨሳል ሌላው ቀበሌ ደሞ ተቀብሎ ለቀጣዩ ቀበሌ የሚታይ ቦታ ላይ ያጨሳል እንዲህ እያለ ደቡብን ሊያደርስ ይችላል። እንዲህ ኣይነት ዘዴዎች በህዝቡ ባህል ውስጥ ስላሉ በቀላሉ ዓመጹን ማዳራስ ይቻላል። በከተማው ደሞ የተለየ መልክ ያለው ዘዴ መፍጠር ያሻል።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
geletawzeleke@gmail.com
ገለታው ዘለቀ

http://www.ethiopianreview.com/research/5539

http://en.wikipedia.org/wiki/Nonviolent_resistance

http://www.ethiopianreview.com/amharic/?p=60193

Advertisements

Posted on December 19, 2012, in Politics and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s