ፖለቲካ ምርጫ እንጂ አማራጭ አይደለም!

መጽሐፍ ቅዱስ “ባለንጀራህን በማለዳ መመረቅ የመርገም ያክል ነው” እንዲል እኛ ደፍሞ ጥሎብን አዲስ ወጣኒ ሲገኝ (በተለይ  አጀንዳችንን የሚደግፍ) ክቡር: ንዑድ: ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ምሁር: ባለ ብዙ ተመክሮ: አልሞ ተኳሽ – እፍ ብሎ ፈዋሽ:  በሰማይ እንደ ንስር በምድር እንደ ባቡር … እየተባለ እንዲሁ ጊዜ ወስደን ግራ ቀኙን አይተን ሳናጣራ በቀድሞ በደሉ ተተጸጽቶም የንስሃ ጊዜውን ሳይጨርስ በታላቅ ጭብጨባና ጩኸት “ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ” በማለት ራሳችንን ለእንግዶች አሳልፈን በመስጠት ማንም አያክለንም:: ታድያ በዚህ መንፈስ ክበን ያወጣናቸውንና ያነገስናቸውን ወገኖች ሳይውሉ ሳያድሩ በሆነ ምክንያት ደግሞ አዋክበንና በጣጥሰን ለመጣልም እንዲሁ አቻ የማይገኝልን መሆናችን በእውነቱ እጅግ እሳዛኝ ገጽታችን ነው::

ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ማንኛውም በውጥን የፖለቲካ አዙሪት  የሚሽከረከሩ:  በሰላም ወጥተህ መግባት የማይቻልባቸው: ዜጎች የመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ በገዛ አገራቸው እንደ ምጻተኛ በመንቀጥቀጥና በታላቅ ፍርሃት ተውጠው ከሚኖሩባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር ሰለባዎች የሆኑት የአፍሪካ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ድሃ አገሮች አንዷ ናት:: ለዚህ ሁሉ ሀገራዊ ችግር: የዜጎችም ግፍና ውርደት ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ስብእና ተጠቃሽ ነቀርሳ ነው:: ለምን?

ü ፖለቲካ በዚህ ስላልተሳካ እስቲ በዚህ ደግሞ ይሞከር ተብሎ የሚገባበት ዓይነት የስራ መስክ ስላይደለ::

ü  ፖለቲካ ነገሮችን የመያዝና የመልቀቅ ሂደት እንጂ አቅጣጫ ሳይለይ የሚነፍሰውንን ነፋስ እየተከተልክ ሕዝብንና ሀገርን ማወክም አለመሆኑ::

ü  ፖለቲካ ሕዝብን የማገልገል ሽክም/የአደራ ስልጣን እንጅ ስምህን የምትገነባበት መድረክም አለመሆኑ::

ü በተጨማሪም በትርፍ ሰዓት ለመረበሽ/ለማወክ ካልሆነ የትርፍ ሰዓት ብሎ ፖለቲከኛ (መሪ) አለመኖሩ ነው::

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ የቀጨጨው: ፍሬ አልባ በለስ በመሆንም እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ የሚጎተተው ምክንያቱ  ይሄ ነው:: ከፍ ስንል በዝርዝር ከተመለከትናቸው ጥቂት ነጥቦች በተጨማሪ አሁን ያለውን የሀገሪትዋ ፖለቲካና የፖለቲከኞቻችን ወቅታዊ ገጽታ መያቱና መቃኘቱ ጠቃሚ ይመስለኛል:: ይኸውም ከፊታችን እየተሻገሩ የሚገኙትንና ያሉትን፥ (ነጥቦቹ አንድስንኳ የለም በሚል በደፈናው ሁሉን በአሉታዊ እይታ የመፈረጅ መንፈስ የለውም:: ለምሳሌ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ካልቸው ጽኑ  አቋም የተነሳ ከቀድሞ ስልጣናቸው ራሳቸውን ያገለሉ/የተነሱ አይመለከትም)

 • በአቅም ማነስ የተፈነገለ፥ እነዚህ ምንም እንኳን በፖለቲካ ስልጣን አከባቢ በመሪነት ቦታ ላይ ባይቀመጡም በዋናነት የሕዝብን ሰላምና አንድነትን በሚያናጋ መልኩ ክፉ ወሬን በመፍተልና በመንዛት ክፉኛ የተጠመዱ ወጊድ ሊባሉ የሚገባ ለቃሚዎች: አጥፍቶ ጠፊዎችም ናቸው:: በእስራኤል (በይሁዳም ሆነ በኢየሩሳሌም) የነገሱ ክፉዎችም ደጋጎችም ነገስታት በሚገርመው
  ሁኔታ አንድ የሚያደርጋቸው ነጥብ ቢኖር ወረኛን አለመውደዳቸው ነበር:: ወደ ስልጣን ሲወጡም የመጀመሪያ ስራቸው ዋሾ ምልስና ቀላዋጭ ብዕርተኛ ከግዛታቸው መጥረግ ነበር:: ዛሬ በመካከላችን በየድረ ገጹና መገናኛ ብዙሐኑ በቃልም በጽሑፍም ቀዋሚ ተሰላፊዎች ሆነው የአንበሳ ድርሻ የያዙ የሰው ልጆችን (የዜጎችን) ስብእና ለመልካም ነገር በመቅረጽና አእምሮን በማጎልበት ረገድ በየትኛም መለኪያ/መመዘኛ ሚዛን የማይደፉ “እገሌ እገሌን ገደለው: እገሊት ከእገሌ አየሁት/ኋት” የሚሉትንና ሌሎች በርካታ አሳፋሪ ተራ የሰፈርተኛ ወግና ሀሜት ይዘው የሚክለፈለፉትን ነው:: እንዲህ ያሉትን ጥቃቅን ቀበሮዎችን የማጥመድ ድርሻ የዜጎች ሁሉ ግዴታ ነው!

 

 • ሲቆላምጥ ከስልጣኑ የተባረረ፥ እነዚህ ሰዎች ባይደረስባቸው/ባይባረሩ ኖሮ ዛሬም ገዳዮቻችን ነበሩ:: ብዙ ነገር የለመደች ነፍስ እንደሆነች ከሕዝብ ጫንቃ ላይ በቀላሉ ትገላገላለች ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው:: ከስህተታቸው ተምረው እንደማንኛው ዜጋ መኖር ማለት ለእነዚህ ሰዎች የሞት ሞት በቁማቸውም የመቀበር ያክል ትልቅ ውረደት ሆኖም ሲለሚታያቸውና ስለሚሰማቸው “እናቱ የሞተችበትና እናቱ ገበያ የሄደችበት እኩል አለቀሱ/ያለቅሳሉ” እንደሚባለው እንባ እንኳ መለየት አቅቶን ዛሬም ተንገዳግደው እያንገደገዱን ይገኛሉ:: ታድያ ባለቤት የሌለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የእንዲህ ዓይነት ሰዎች መፈንጫና መጫወቻ ሲሆን ማየት ምን ይደንቃል?

 

 • ሮጦው መቅደም ሲያቅታቸው የወደቀውን ለመቀጥቀጥ ያደቡ ቀቢጸ ተስፋዎች፥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ  የመቻቻል መሆኑ ቀርቶ የቂም: የበቀል: የመናቆርና የመገዳደል በመሆኑ ተጠያቂው እኛው ራሳችን ነን!! በሚያስፈልገን ዓብዪ ጉዳይ ላይ ከማተኮርና መክፈል የሚገባንን መስዋእትነት በመክፈል አሳደን የራሳችን ከማድረግ ይልቅ በምንፈልገው ነገር ላይ ተጠምደናልና:: አቋራጭ ቁልቁል የሚያወርድ ገዳይ መንገድ እንጅ ከጉድጓድ የሚያወጣ መሰላል ለመሆኑ የምንገኝበትን አስከፊና አሳፋሪ ሁኔታችንን ካላስተማረን ከወዴት እንማር ይሆን?

 

 • በቃርሚያው ዘመቻ ከጨወታ ውጭ ሆነው የከሰሩትን ፖለቲካ የሚባልውን የሕዝብ ሸክም ፈጽሞ ያልዋለባቸውን ሌላ ተጨማሪ በሽታ ገዝተናል፥ እንግዲህ ወደድንም ጠላንም
  እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ በርካታ ነጥቦች ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ዕድገት ማነቆዎች ናቸው:: በአጠቃላይ የሀገራችን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሄጃ: መጠሊያና መሸሸጊያ ያጣ: የከሰረ ኪሳራውን ለማካካስ: ቂመኛ ቂሙን ለመወጣት የሚሰበሰብበት ባለቤት የሌለው የቆነቆነ ጎተራ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም:: ታድያ ምን እናድርግ?

ከዚህ ቀደም በጥቂቶች ዘንድ እምብዛም ያልተወደደ “እውነተኛ የሕዝብ ፍቅር ያላቸው ነፃ አውጪዎች እነ ማን ናቸው?” ስል ስንዴውን ከንክርዳድ: በጉን ከፍየል: እውነተኛውን ከአስመሳዩ መለየት ይቻለን ዘንድ እንዲሁም ሀገርንና ወገንን በሚረባ መልኩ እንዴት ባለ መመዘኛ  የፖለቲካ መሪዎችን መከተልና መደገፍ እንደሚገባን በማከል ሃሳቤን ማካፈሌ የሚታወስ ሆኖ  አሁን ደግሞ

ü  ደማቸው ቢመረመር ምናቸውንም ቢፋቅ የሕዝብ ልብ ያላቸው፥

ü  በቃልም በስራም የታመኑ፥

ü  ከተራ ፕሮፖጋንዳ የጸዱ፥

ü  በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድነትና በመቻቻል በወንድማዊ ፍቅርም የተገነባችውን አገር በቀጣይነት የማስተዳደርና የመምራት ልብና ጽኑ እምነት ያለው መሪ የማፍራትና የማውጣት በአንጻሩ ደግሞ

 • አፍራሽ አጀንዳ ያለው:
 • ካዝናው አይጉደልበት እንጂ ሀገርን ከመሸጥ ዜጎችን ከመበተን ወደኋላ የማይል፥
 • ጥርሱ ነክሶ ቂም ቋሮ ሲያበቃ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ለበቀል ያደባውን፥
 • ኪሳራውን በፖለቲካ ስም ለማካካስ የሚያቋምተውን፥
 • በአደባባይ የኢትዮጵያ አንድነት እንደሚያምኑ እያወጁ ውስጥ ለውስጥ በሚተላለፉ የኤሊክትሮኒክስና ሌሎት መልእክት መለዋወጫ መንገዶች እየተጠቀሙ ደግሞ የኢትዮጵያ
  አንድነትን ፈጽመው የማይቀበሉ በአንጻሩ ጉራጌነትን: ኦሮሞነት: ትግሬነት: አማራነትንና ወዘተ የማይበጀንን ጎጠኝነትን የሚሰብኩን፥
 • የሚያስፈልገን ፍትሐዊ የሆነ በህግ የበላይነት የሚያምንና የሚገዛ መንግስታዊ አስተዳደር ነው:: ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ መሪዎች ሚና መጠቋቀም ሳይሆን ጊዜአቸውንና ጉልበታቸውን ማጥፋት የሚገባቸው በግለሰቦችን ላይ ቂም ከሚቋጥር ይልቅ በስርዓቱ አገዛዝ ላይ ያነጣጠረ: አንድ ልብ የሆነ ሕዝብ: በአንድነት የሚያምን ዜጋ ካልተቻላቸው ድምጻችንም ሆነ ድጋፋችንን የመንፈግና የመንሳት የመላዕክት ወይንም ደግሞ የምዕራባውያን ድርሻ ሳይሆን የእኛ የሰለባዎቹ የኢትዮጵያውያን ግዴታ መሆኑ አውቀን በምንም ዓይነት መልኩ በአድሉአዊነት ክፉ መንፈስ ሳንጭበረበር በነቃ አእምሮ ራሳችንን ችለን እንደ ባዕድም ሳይሆን እንደ ባለቤት በልበ ሙልነት ወሳኙ ሚና መጫወት ስንችልና ተሳትፎአችንን በሟጧጧፍ አንድነታችንን ስናረጋግጥ ብቻ ነው:: አመጸኛ እንደሆነ ምን ጊዜም ቢሆን አመጻኛ ነውና!

በተጨማሪም የፖለቲካ ስልጣን ባለቤት ሰፊው ሕዝብ ነው (በብዙሐኑ እጅ ነው) ሲባል ሌላ ማለት ሳይሆን በእያንዳንዳችን እጅ ያለውን: ይህ ማለት ወደን (በጎሳ በፓርቲ ስም ተታለን) ካልሰጠ አንድም ባለማወቅ ካላባከንነውንና በከንቱ ካላመከንነው በስተቀር ማንም እጃችንን ጠምዝዞ የማይወስድብን የማይቆረስ የማይቀነስ ሀብት ባለቤት መሆናችንን አውቀን በእጃችንን ያለውን ሀብት ስንጠቀምበት ነው::

ለመሆኑ ይህን ያውቁ ኖሯል?

ü  ንግድን ሟጣጣፍ: ሀብት ማካበትና ማትረፍ ማለትና ሕዝብን ማገልገል ማለት ሁለት ጽንፍ መሆናቸውን ያውቁ ኖሯል? እንግዲህ ለሁለቱ ስኬት ግለሰቡ ሊከታላቸው የሚገባውና የሚጠበቅበት መርሆችም እንዲሁ ለየቅል ናቸው:: የንግድ ስሌት በሕዝብ አገልግሎት  አስተዳደር ላይ  አይሰራምና! በንግድ/በኢንቨስትመንት ዓለም የተሳካለት ሁሉ የሀገር መሪ ይሆናል ማለትም አይደለም:: ስኬት ሌላ ነው ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ቦታ ማስቀመጥ ደግሞ ሌላ ነውና::

ü  ሌላው የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን በማወቅ (ሩጫም ቢሆን) የግል ሀብት ማካበት/የከፍተኛ ነዋይ ባለቤት መሆንና ያለ አድልዎ ሁሉን ያማከለ ፖሊሲ ነድፈህ ሀገርንና ሕዝብን መምራት ማለት ደግሞ ሰሜን ከደቡብ ምዕራብም ከምስራቅ እንደሚርቅ እንዲሁ መሆኑ ያውቁ ኖሯል?

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

yetdgnayalehe@gmail.com

http://www.ethiopianreview.com/amharic/?p=56273

Advertisements

Posted on December 21, 2012, in Human Right, Politics and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s