ሦስቱ ባዶ ወንበሮች

ወንበር እና ዙፋን ብዙ መገለጫ አለው። ወንበር ሲባል ሁላችን ራሳችንን የምናሳርፍበት ማንኛውም መቀመጫ ማለት መሆኑ እንዳለ ሆኖ “ወንበር” ብዙ አንድምታ እንዳለው እናውቃለን።

ለምሳሌ ፍርድ ቤት ገብተን “የግራ ወንበር፤ የቀኝ ወንበር” ሲባል ብንሰማ ትርጉሙ “የግራ ዳኛ፣ የቀኝ ዳኛ” መሆኑ ይከሰትልናል። ምናልባት ወደ አብነት ት/ቤት (ቆሎ ት/ቤት) ጎራ ብለን “ወንበር ተዘርግቷል፤ ወንበር ታጥፏል” ሲባል ብንሰማ “ትምህርት ተጀምሯል፣ ትምህርቱ ተጠናቋል” ማለት ነው። “እገሌ ወንበር ተከለ” ከተባለ ደግሞ “መምህር ሆነ፣ አንድ የትምህርት ዘረፍ ለማስተማር ጀመረ” ማለት ይሆናል። ሥልጣን ባለበት አካባቢ “እገሌ የእገሌን ወንበር ይፈልጋል” ከተባለ …. ያው … ሥልጣንም ከሆነች፣ ኃላፊነትም ከሆነች … ሊቀማ የተዘጋጀ አለ ማለት ነው።

አንድ ታሪክ

እዚህ በአሜሪካ የምርጫ ፉክክር ሰሞን ሁለት ታላላቅ የፓርቲዎቹ ጉባዔያት ተካሂደው ነበር። የሁለቱም ፓርቲዎች ዓመታዊና ፕሬዚዳንታዊ እጩዎቻቸውን የሚያጸድቁባቸው ወሳኝ Ethiopian PM Hailemariam Desalegn and the empty chairጉባዔዎች። ታዲያ፣ ከሁለቱ በአንዱ፣ በሪፐብሊካን ዓመታዊ ጉባዔ ላይ “ራምኒን ለማስተዋወቅ፣ ተመራጭ ለማድረግ” የቀረቡት ዝነኛው የሆሊውድ ኮከብክሊንት ኢስትዉድ (Clint Eastwood) ንግግራቸውን ሆሊዉዳዊ ድራማ አስመስለው ቀርበዋል። ሰውየው በንግግራቸው ጣልቃ፣ ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር ክርክር ቢጤ ያደረጉበት ትዕይንት አስደማሚ ነው። በርግጥ ኦባማ በቦታው አልነበሩም። እርሳቸውን እንዲተካ የተደረገው ገጸባሕርይ “ባዶ ወንበር” ነበር። ኢስትዉድ ሲያወሩ ወደ ወንበሩ እየዞሩ “እንደ ሰው” እያናገሩት ነበር። እናም በትዕይንቱ የተሳለቁ ሰዎች “Obamachair” የሚል ቃል ፈጥረው (ObamaCare የሚለውን ለውጠው) ሲዘባበቱባቸው ሰንብተዋል። “ካረጁ አይበጁ” እያሉም አሹፈውባቸዋል። ወደ ኢንተርኔት ገባ ብላችሁ “ኦባማቼር” ብትሉ ጉዱን ታዩታላችሁ።

ሌላ ታሪክ

እንዲህ በዐቢይና ታላቅ ጉባኤ ላይ በክብር የሚቀመጥ “ባዶ ወንበር” የማውቀው በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅ/ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ነው። ጉባዔው በፓትርያርኩ መሪነት የሚስተናበር ቢሆንም መሪውና ወሳኙ መንፈስ ቅዱስ ነው ከሚለው አስተምሮ በመነሣት በጉባዔው ውስጥ በመጎናጸፊያ የከበረ አንድ ባዶ “ዙፋን” እንደሚቀመጥ አባቶች ይናገራሉ። ወንበሩ ከርዕሰ ጉባኤው፣ ከጉባዔው ሊቀ መንበር፣ ከፓትርያርኩ ጀርባ ይቀመጣል። ማንም ሰው አይቀመጥበትም። መንፈስ ቅዱስ የጉባዔው አካልና መሪ መሆኑን ያጠይቃል። “ባዶው ወንበር” ተምሳሌታዊ ብቻ ሳይሆን አማናዊ ትርጉም ያለው ሐሳብ ነው። በሌሎቹ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም ይሁን ሲኖዶሳውያን በሆኑ ካቶሊክን በመሳሰሉ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህ ትውፊት ይኑር አይኑር አላወቅኹም።

የአቶ ኢስትዉድ ባዶ ወንበር እና ሃይማኖታዊ ትርጓሜ ያለው የቤተ ክርስቲያን “ባዶ ዙፋን” በይዘትም፣ በተምሳሌትም ይለያያሉ። የመጀመሪያው “ወንበር” ለጊዜው በዚያ ቦታ ያልተገኘ ሰውን ወክሎ እንዲጫወት የተደረገ ገጸ ባሕርይ ሲሆን ሁለተኛው ግን በርግጥም “እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አለ፤ ይመራናል” ብሎ በማመን የሚደረግ ነው።

ሦስተኛ ታሪክ

ታዲያ የባዶ ወንበር ነገር ለሦስተኛ ጊዜ ራሴን “ቂው” ያደረገኝ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ም/ቤት ተገኝተው መልስ ሲሰጡ የተቀመጡበትን ቦታ ባየኹ ጊዜ ነው። “ምናልባት አቀራረጹ ይሆን?” ብዬ አተኩሬ ለማየት ሞከርኩ። በርግጥም አቶ ኃ/ማርያም የተቀመጡበት ቦታ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በሚቀመጡበት ቦታ አልነበረም። የአቶ መለስ “ወንበር” (ሁለተኛው ተርታ ቁጥር አንድ) ባዶዋን ቁጭ ብላለች። ደርሶ ተቺ፣ ደርሶ ነቃፊ ላለመሆን ለራሴ ሁሉንም ሎጂካዊ አመክንዮዎች ለማየት ሞከርኩ። በዚህም ብል በዚያ ያቺ “ወንበር” ባዶ የሆነችበት ምክንያት ግልጽ አልሆነልኝም። መቸም እንደ አቶ ኢስትዉድም፣ እንደ ቅ/ሲኖዶሱም እንዳልሆነ እናውቀዋለን። ታዲያ ለምን ባዶ አደረጓት?

በየትኛውም የሥልጣን ወንበር ላይ ለሚቀመጥ ሰው፣ እርሱ በሚያልፍበት ጊዜ ተተኪው በርሱ ቦታ እንደሚቀመጥ፣ እንኳን ዛሬ “ዲሞክራሲያውያን” ነን ብለን ቀርቶ በነገሥታቱም የተለመደ ነው። “ተቀመጥ በወንበሬ፣ ተናገር በከንፈሬ” እንዲል “መተካካቱ” ሲመጣ ከነሙሉ ክብሩና ግዴታው ሁሉ እንጂ በግማሹ አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትር የመተካት ልምድ የሌላት አገራችን እርሟን ከዚያ ሰዓት ስትደርስ የትኛውን ጥላ የትኛውን እንደምታንጠለጥል የቸገራት ይመስላል። በሌሎች ጉዳዮች ሲሆን “በሕንድ እንዲህ ሲደርግ ዓይተን ነው፣ ጎረቤታችን ኬኒያ እንኳን እንዲህ ነው የምታደርገው፣ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ስዊዘርላንድ እንዲህ ናት” እንደሚባለው በዚህ ጉዳይ ማጣቀሻ ለመፈለግ የተሞከረ አይመስልም።

በመጀመሪያ። የጠ/ሚኒስትሩ ቤተሰቦች ቤተ መንግሥቱን ለአዲሱ ጠ/ሚኒስትር ላለማስረከብ “ግብግብ” መግጠማቸውን “ጠላት የሚባለው ዳያስጶራው” ብቻ ሳይሆን “የታመኑ የውጪ አገር ፈረንጅ ጋዜጠኞች” ሳይቀሩ ሲተቹ ሰንብተዋል። እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ ግለሰብ ሳስበው እንኳን 20 ዓመት 2 ዓመት ከምኖርበት አፓርታማ ስቀይር እንዴት እንደሚከብድ አውቀዋለኹ። “ይኼ ሁሉ ዕቃ መቼ የሰበሰብኩት ነው?” ማለት የተለመደ ነው “ልሸክፍህ” ሲሉት። የሆነው ሆኖ የቤት ርክክቡ “ሰላማዊ” በሆነ መንገድ መጠናቀቁ ተገቢም፣ የሚጠበቅም ነው።

ቤቱ ይለቀቅ እንጂ፣ እንደማንኛውም የመሪ ቤት “የሚነቃነቁ” እና “የማይነቃነቁ” ነገሮች መኖራቸው ይታወቃል። መተካካት ስለተባለ ብቻ ኋላ የመጣው የፊተኛውን ጫማና ኮት አድርግ አይባልም። የፊተኛው ሲጠቀምባቸው ከነበሩት ዕቃዎች መካከል ለመታሰቢያነት በሙዚየም ሊቀመጡ የሚገባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። አገሪቱን 20 ዓመት ያስተዳደሩት ጠ/ሚኒስትር (እንደተባለው በስማቸው ሙዚየም የሚቆም ከሆነ) ይጠቀሙባቸው የነበሩት የቢሮ ዕቃዎች ወዘተ ወዘተ መሰብሰባቸው አይቀር ይሆናል።

ይሁን እንጂ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር መንግሥታዊ ኃላፊነትን በሚረከቡበት ወቅት ከነሙሉ ክብሩ እንጂ በጎዶሎነት መሆን አይገባውም። በፓርቲ ሥርዓታቸው ለቀድሞ የፓርቲ ሊቀመንበራቸው ክብር ሲሉ የፓርቲያቸውን “ወንበር ባዶ” ማድረግ ይችላሉ። የመንግሥት ሥልጣን ግን አገራዊ እንደመሆኑ ለግለሰቡ የሚሰጠው ክብር የሰውየውን ማንነት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ መሆን አለበት።

እውነቱን ለመናገር የፓርላማው ባዶ ወንበር ከቀጥተኛ ትርጉሙ ይልቅ ተምሳሌታዊነቱ (Symbolism) የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል። አቶ ኃ/ማርያም በመለስ ወንበር አለመቀመጣቸው ብቻ ሳይሆን ያልተረከቡት ሌላም ብዙ ነገር እንዳለ ማሳያ ይመስላል። ቢሯቸውስ “ግዴለም የድሮው ቢሮዬ ሆኜ እሠራለዅ” ወይም “አንዲት ወንበር በጎን በኩል አስቀምጡልኝ” ብለው በደባልነት ገብተው ይሆን?

“ከልት”/Cult መፍጠር

ሳስበው ሳስበው መለስን “ኢትዮጵያዊው ኪም ኤል ሱንግ” ለማድረግ እየተሠራ ይመስለኛል። ኪም ኤል-ሱንግ እ.ኤአ. ከ1948-1994 ድረስ የአገሪቱን አመራር ጨብጠው የዘለቁ መሪ ነበሩ። ከ1948-1972 ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከ1972-94 ደግሞ ፕሬዚዳንት ነበሩ። እርሳቸው በሥልጣን ላይ ብቻቸውን በተቀመጡባቸው ዓመታት አሜሪካ 10 ፕሬዚዳንቶችን፣ እንግሊዝ 14 ጠ/ሚኒስትሮችን፣ ሶቪየት ኅብረት ሰባት መሪዎችን፣ ጃፓን 21 ጠቅ/ሚኒስትሮችን፣ ጎረቤቷ ደ/ኮሪያ 6 ፕሬዚዳንቶችን አስተናግደዋል።

ሞት አይቀርምና ሲሞቱ ልጃቸውን ለልጃቸው አሸጋግረው አልፈዋል። እርሳቸው በበኩላቸው “ታላቁ መሪ”፤”The Great Leader” (በኮሪያኛ Suryong) የሚል ቅጽል ተቀጽሎላቸዋል። ከዚያም ባሻገር በሕገ መንግሥት ደረጃ የተቀመጠ የአገሪቱ “ዘላለማዊ ፕሬዚዳንት” ተብለው ተሰይመዋል። የልደት ቀናቸውም ከዓመታዊ አገሪቱ በዓላት እንደ አንዱ በይፋ እንዲከበር ተሰይሟል።

በየአደባባዩ፣ በየታላላቅ ሕንጻዎች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ በምክር ቤት ወዘተ ወዘተ ፎቶግራፋቸውን ከመደበኛ ይዘት እጅግ ከፍ ባለ መጠን እያሳተሙ መስቀል የገጽ ግንባታ ሳይሆን “ከልት”/Cult መፍጠር ነው። አሁን ባለው ይዘት መለስ ዜናዊን ኪም ኤል-ሱንግ ማድረግ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለቤተሰባቸው ክብር አይሆንም።

“የመለስ ራእይ” ከሚለው ጀርባም የሚኖረው ይኸው “ዘላለማዊነት” የተመኙለት መሪ እና ኢትዮጵያዊ-ኪም አል ሱንግ የመፍጠር ሐሳብ ነው። ፓርቲው “ራእዩ” በትክክል የገባቸው እና ያልገባቸው፣ ራእዩን የተቀበሉና ያልተቀበሉ፣ የራእዩ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች በሚል ፍረጃ ውስጥ ለመግባት አፋፍ ላይ ይመስላል። ነገ ማንም ሰው ያለምንም አመክንዮ “ራእዩን ባለመደገፉ ብቻ” ወንጀለኛ ሊባል ይችላል። ኢሕአዴግ የታገለው የፓርቲ ዓላማ ነበረው። መለስም ያንን አይተው ነው የፓርቲው አባል የሆኑት። አሁን ግን መመሪያቸው የመለስ ራእይን መቀበል እና አለመቀበል “ማስቀጠልና አለማስቀጠል” ሆነ ማለት ነው?

በነገራችን ላይ “ማስቀጠል” የሚለው ቃል ሁሌም ያስፈግገኛል። ቋንቋ ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል በሚለው የሥነ-ቋንቋ ሀ-ሁ እንዳምን ከሚያደርጉኝ ነገሮች አንዱ እንዲህ ያሉት ቃላት ናቸው። “ማስቀጠል” የሚል ግስ ተፈጠረ ማለት ነው? ለነገሩ ሁሉም “አስቀጣይ” ከሆነ ማን “ቀጣይ” ሊሆን ነው? ቃሉን “መገደብ” በሚል ብትተረጉሙት ሁሉም “አስገዳቢ” ከሆነ ማን “ገዳቢ” ሊሆን ነው። ሁሉ ከሆነ ቃልቻ ማን ይሸከማል ስልቻ አለ ያገራችን ሰው።

ይቆየን – ያቆየን።

ECADF.COM

Advertisements

Posted on December 30, 2012, in News, Politics and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s