መንግሥትና ቤተ ክህነቱ፣ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የቀጠለው ድርድር፣ የፓትርያሪክ ምርጫ ውዝግቡ ወዴየት እያመራ ይሆን!?

 

Abuna Merkorios Patriarch of the Ethiopian Orthodox Church

እሁድ ታህሳስ 21 ቀን በቶሮንቶ በተከበረው አመታዊው የታህሳስ ገብርኤል በዓለ ንግስ ላይ ፓትሪያርክ መርቆሬዎስ ለህዝቡ ቡራኬ ሲሰጡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ሚሊዮን ሚቆጠር ምእመናን እንዳላት ይታመናል፡፡ ይህች አንጋፋና ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ታላቅ ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ መሠረት ለመሆን የቻለች የሃይማኖት ተቋም ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት የነበራት ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡ ይኸው ሚናዋ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ጃማይካና ካረቢያ ድረስ ተሻግሮ ለብዙ ሚሊዮን የምድራችን ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ፋና ወጊ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ሆና ለመቆጠር የበቃችበትን ልዩ ታሪካዊ ክብርና ሥፍራን ለመጎናጸፍ አስችሏታል፡፡

ይህን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለነፃነት፣ ለፍትህ እና ለሰው ልጆች እኩልነት መስፈን የነበራትን ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ የሆነ ጉልህ ሚና በተለይ በደቡብ አፍሪካውያን የጸረ-ባርነትና የጸረ-አፓርታይድ ትግል ወቅት ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ፋኖዎች እንደ ትልቅ ስንቅና ወኔ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ይህን ታሪካዊ እውነታ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ታቦ ኢምቤኪ እ.ኤ.አ በ2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ የክብር ዶክትሬት በሰጣቸው ወቅት ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸው እንዲህ በማለት ነበር በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ራሳቸውን ጨምሮ፣ አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ የሚሰማውን ክብርና ኩራት በእንዲህ መልኩ የገለጹት፡-

…Thus would the authentic African Church serve as a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity.

The African National Congress of South Africa, the oldest modern national liberation movement on our continent, was born out of our country’s Ethiopian Churches. Indeed the African nationalism which drove our national liberation movement was described as Ethiopianism.

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊትና ጥንታዊ የሆነ እምነቷ፣ ሥርዓቶቿና ትውፊቶቿ እንደ ሌሎች አፍሪካ አገራት የምዕራባውያን ቀኝ ገዢዎች አሻራ ያለረፈበት በመሆኑ Reconciliation within the Ethiopian Orthodox Tewahedo Churchአፍሪካዊት እናት ቤተ ክርስቲያን (An Independent African Mother Church, African Indigenous Church)የሚል ክብርና ቅጽል እንድትጎናጸፍ አድረጓታል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ኢትዮጵያውያኑ ነገሥታትና ሊቃውንት ክርስትናውን ከሕዝባቸው ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ልማድና ትውፊት ጋር በማጣመር ውብና ማራኪ እንዲሆን አድርገው እንዳቆዩት በርካታ መርጃዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

ዛሬ በሌላው ክርስቲያን ዓለም የማናየውን ይህን ጥንታዊና ሐዋርያዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ባህልና አምልኮ ምዕራባውያኑ ቱሪስቶችና ተጓዦች ብዙ ሺህ ዶላራቸውን ከስክሰው ሊያዩት በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋሉ፡፡ ይህ ልዩ የሆነው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊው ሥርዓቷ፣ የወንጌል መሰረት ያለው ክርስቲያናዊ ባሕሏ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ምእመኖቿ እና ተከታዮቿ የኢትዮጵያዊ ማንነትና ብሔራዊ ኩራት መገለጫ ሆኖ የመዝለቁ ምስጢር ይኸው ይመስለኛል፡፡

በተመሳሳይም የእስልምና ሃይማኖትም ብንመለከት ምንም እንኳን ከሌሎች አገራት ቀድሞ ወደ አገራችን የመጣ ቢሆንም ሃይማኖቱ ልክ እንደ ክርስትናው ሁሉ በኢትዮጵያዊ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ወግና ትውፊት ላይ ውብ የሆነ ጥምረትን ፈጥሮ ነው እዚህ የደረሰው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ‹‹የሃይማኖቶች መቻቻል ምድር›› ተብላ እንድትጠራ ያደረገውም እነዚህ ሁለት አንጋፋ ሃይማኖቶች በማይበጠስ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነት፣ የጋራ ታሪክ፣ ባሕልና ቅርስ ላይ የተሳሰሩ በመሆናቸው ይመስለኛል፡፡

ከዚህም የተነሳ ኢትዮጵያያን ሙስሊሞች እንደ ሌላው ዓለም ወይም በታሪክ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ልዩ ትስስርና ቅርበት ካለን ግብፅም ሆኑ ሌሎች ጎረቤቶቻችን አፍሪካውያን አገሮች የእስልምና ሃይማኖቱን ብቻ እንጂ የዐረባዊነትን ቋንቋና ባህል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሊለብሱትና ሊወርሱት አልፈቀዱም፡፡ ይኽም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የተለዩ ያደርጋቸዋል፡፡

እንደ እስልምና ሃይማኖት ምሁራን አገላለፅ (Ethiopians only Islamized but not Arabized) በማለት በአጭር ቃል ታሪካዊ እውነታውን ይገልጹታል፡፡ ይህም ሕዝባችን ስላለው ጠንካራ ብሔራዊ ማንነትና ኩራት እንዲሁም ዘመናት ያላደበዘዙት የጋራ ታሪክና ቅርስ ያለው ኩሩ ሕዝብ እንደሆነ ትልቅ ማሳያ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ዓይነት ሃይማኖት ቢኖረው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅርና በእግዚአብሔርም ላይ ያለው እምነት ጠንካራ ነው። የበርካታ ተጓዦችና አጥኚዎች በጥናታቸው ‹‹ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛ ሕዝቦች የሚበዛባት አገር ናት፡፡›› ወደሚለው ድምዳሜ የሚያደላ ነው፡፡

ይህ ሕዝብም በታሪኩ ሃይማኖቱን የራሱና የግሉ አድርጎ በአንድ ኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተዋዶና ተከባብሮ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህም ከራሱ አልፎ ለሌላው ዓለም ተምሳሌት የሆነበትን እርስ በርስ ተዋዶና ተከባብሮ የመኖርን አንጸባራቂ ታሪክ የፃፈ ሕዝብ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የምንኮራበት የሁለቱ አንጋፋ የሃይማኖት ተቋማት ታሪክ ሙሉ በሙሉ አልጋ በአልጋ ነበር ብለን እንዳንደፍር የሚያደርጉ በተለያዩ ዘመናት በሁለቱ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የተከሰቱ መለያየቶች፣ ግጭቶችና ጦርነቶች በአገራችን ታሪክ መዛግብት ውስጥ ተመዝግቦ አለ፡፡

በሃይማኖትና በፖለቲካ አላቻ ጋብቻ፣ የተፈጥሮ ሀብትና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ምክንያት ያደረጉ በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖቶች ሕዝቦች መካከል የተነሱ ጦርነቶችና ግጭቶችም እንደነበሩ ማስታወስም ግድ ይለናል፡፡ እነዚህን በአገራችን ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የተነሱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን መንስዔያቸውን፣ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤታቸው ለመተንተን የሚሞከር አይሆንም፡፡

አነሳሴም በኢትዮጵያ ውስጥ አንጋፋ ስለሆኑት ስለ ክርስትና እና እስልምና ሃይማኖት የአብሮነት ታሪክና ግጭት ለመተንተን አይደለም፡፡ ለመግቢያ ያህል ስለእነዚህ ሁለት አንጋፋ ሃይማኖቶች የጠቀስኩት ለጽሑፌ ጥሩ መንደርደሪያ፣ ግልፅና መጠነኛ የሆነ ታሪካዊ እይታን ይሰጠናል በሚል ቅን ግምት ነው፡፡

የዛሬው ጽሑፌ ዋና ማጠንጠኛ አሳብ የሚከተሉት ናቸው፡-

  • የመንግሥትና የቤተ ክህነቱ ጋብቻና ፍቺ ምን መልክ ነበረው፣ አሁንስ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት ምን ይመስላል? የነገይቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ቤተ ክርስቲያን የመምራት ኃላፊነት የማን ይሆናል?
  • ለቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት መከፈል ምክንያት ናቸው የተባሉት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን እልፈት ተከትሎ በስደት ከሚገኙት አባቶች ጋር የተጀመረውን ድርድር ወደ ፍፃሜ ለማድረስ እየተደረጉ ያሉ ውይይቶችስ ምን ፋይዳ ሊኖራቸው ይችላል?
  • እንዲሁም የቀድሞው ፓትሪያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ፣ ወይስ ሌላ ፓትርያሪክ ይመረጥ በሚሉትና፤ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ የነገ ዕጣ ፈንታ ዙሪያ እየተናፈሱ ያሉ ስጋቶችና ፍርሃቶች መነሻቸው ምን ሊሆን ይችላል?
  • በፓትርያሪክ ምርጫው ላይ አንዳንዶች ስውር የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ጫና አለ በሚል እየተንሸራሸሩ ባሉ አሳቦችና ስጋቶች ዙሪያ እኔም የበኩሌን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የትናንት በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መልኩ ከሚጠቀሱ ታሪኮቿ በመነሳት በቅን መንፈስ ላይ የተመረኮዘ ጥቂት የውይይት አሳቦችን ለማጫር ነው፡፡

የቤተ መንግስቱና የቤተ ክህነቱ ጋብቻና ፍቺ ከትናት እስከ ዛሬ

የክርስትና ሃይማኖት ወደ አክሱም ግዛት ከገባ በኋላ በወቅቱ ከነበረው የክርስትና መስፋፋት ባህርይ ጋር በተቃራኒው መልኩ የመንግሥት ሃይማኖት የመሆን ዕጣ ፈንታ ነበር የገጠመው፡፡ በአራተኛው መቶ ክ/ዘመን መባቻ ጀምሮ የተጀመረው የቤተ መንግሥትና የቤተ ክህነት ታሪካዊ ግንኙነትና ዝምድና ውሉ የሚመዘዘውም ከዚሁ ታሪካዊ ክስተት ጀምሮ ነው፡፡

ከዛን ጊዜ ጀምሮ በቤተ መንግሥትና በቤተ ክህነት መካከል የነበረውን ግንኙነት ለመተረክ የሚቻል አይደለም፡፡ ስለዚህም በተቻለኝ መጠን ወደ ተነሳሁበት ዋና የጽሑፌ አሳብ የሚያደረሰኝን የቅርቡን ዘመን ብቻ ታሪክ በማንሳት ጽሑፌን ልቀጥል፡፡

የመንግሥትና የሃይማኖት ጋብቻ እስከ 1966ት የደርግ ወደ ሥልጣን መምጣት ድረስ መሪዎች/ነገሥታቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን እንዳለባቸው በሕገ መንግሥት ጭምር የተደነገገ ነበር፡፡

ይህ የቤተ ክህነቱና የቤተ መንግሥቱ ጋብቻ በደርግ ዘመን መንግሥት በግልፅ መፍረሱ ቢገልፅም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ ሕዝቦች ታሪክ፣ ባሕል፣ ሥልጣኔና ቅርስ እንዲሁም የዕለት ተዕለት የማኅበራዊ ኑሮ መስተጋብር ውስጥ ካላት ሰፊ ድርሻና አሻራ የተነሣ መንግሥትና ቤተ ክህነቱ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መንገድ የመሳሳቡ ነገር መጠኑ ቀነሰ እንጂ ሊጠፋ አልቻለም ነበር፡፡

ደርጉ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡›› ባለ ማግስት በወቅቱ የሚያራምደውን እግዚአብሔር የለሽ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት በመደገፍ ረገድ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች እንዳሻው ለማሽከርክር በፈለገበት ወቅት፣ የአንተ ወሰን እስከዚህ ድረስ ነው በሚል በተነሳ አለመግባባት የተነሣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለተኛ ፓትሪያሪክ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ለእስር፣ ለአንግልትና ለሞት እንዲዳረጉ ሆነዋል፡፡

ይህ ለሺህ ዘመናት ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግሥቱ የተቆራኙበት ታሪካዊ እትብት በአንድ ጀምበር ቆርጦ በመጣል ወደፊት ለመራመድ የማይቻል መሆኑን የእዚህ የደረግ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በተጨማሪም በሕዝቡ ፖለቲካዊ ስነ ልቦና ላይ የራስዋ የሆነ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አሻራ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ከዳር አውጥቶ መንግስትን መምራት አዳጋች መሆኑን ይህ የደርጉ አብዮታዊ እርምጃ በግልፅ እውነታውን የሳየ እንደሆነ አስባለሁ፡፡

በሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስነ ልቦና ውስጥ የራሷ የሆነ ትልቅ ተጽእኖ ያላትን ይህችን ተቋም በተዘዋዋሪ መንገድ በእጁ ለማስገባት ደርግ ፈርጣማ ክንዱን ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አሳረፈ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመቆጣጠር በእርሷም በኩል ሕዝቡን ተገዢው ለማድረግ መሪዋን አሰረ፣ ገደለ፡፡ ውጤቱም ዘግናኝ የሆነ የትውልድ እልቂትና ፍጅትን ነበር ያስከተለው፡፡

ይህ የደርጉ እርምጃ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊው መልኩ የቆየው የቤተ መንግሥቱና የቤተ ክህነቱ የግንኙነት ሰንሰለት  በቀላሉ በአንድ ጀምበር ሊቆረጥ አለመቻሉን ሊያሳዩን ከሚችሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አንዱና ተጠቃሹ ነው፡፡

የቤተ መንግሥቱና የቤተ ክህነቱ ተቋማት እርስ በርሳቸው እንደ ተቃራኒ የማግኔት ዋልታዎች የሚሳሳቡበት ምክንያቱ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ሕይወትና ፖለቲካ ውስጥ ከነበራትና አሁንም ካላት ተጽእኖ የተነሳ እንደሆነ ብዙዎች የቤ/ቱ ምሁራንና ታሪክ አጢኚዎች ይስማማሉ፡፡

በዚህና በአያሌ ተዛማጅ ምክንያቶች ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገሪቱ የሚከሰቱ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ እንዳላት ሁሉ እርሷም ከተለያዩ አቅጣጫዎችና ከመንግሥት በሚመጡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኩነቶች ተጽእኖ ስር መሆኗ ግን አልቀረም፡፡ እናም መንግሥትና የቤተ ክህነት ግንኙነት አዎንታዊና አሉታዊ ውጤቱን እያስመዘገበ ዘመናትን ተሻግሮ  አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያጠኑ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ የሆኑ የአንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቋም ባልደረባ እንደሚሉት፣ ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቷ ራሷን ቻለች በተባለችባቸው ሃምሳ ዓመታት ከግብፅ ጥገኝነት ብትላቀቅም በመንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ወደ መሆን መሸጋገሯን፡፡›› በጥናታቸው ይገልፃሉ፡፡

እኚሁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር እንደሚያስረዱት የቤተ ክርስቲያኒቱን የሃምሳ ዓመታት እራሷን የመስተዳደር ጉዞ ‹‹ፍፁማዊው ከነበረው የውጭ ጥገኝነት፣ ፍፁማዊው ወደሆነው የውስጥ ጥገኝነት የተሸጋገረበት ነው፡፡›› በማለት በአጭር ቃል ይገልጹታል፡፡

‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱ ከግብፃውያን ቅኝ ግዛት ተላቃ በንጉሡም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግሥት አንፃራዊ በሆነ መልኩ ውስጣዊ አስተዳደሯን በተመለከተ ራሷን ችላ በነፃነት ማከናወን የምትችልበት ዕድል ማግኘቷን ያሰምሩበታል፡፡ ይህን አንፃራዊ በሆነ መንገድ ራሷን በነፃነት የማስተዳድር ዕድል ከ1983ቱ የመንግሥት ለውጥ ጋራ ሲመጣ ግን ብቻውን አልመጣም፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቷ ራሷን ሙሉ በሙሉ የማስተዳደር አቅሟን በሚገባ ሳታዳብርና በቂ ዝግጅት ሳታደርግ ነበር ነፃነቱ የደረሰባት ይላሉ፡፡›› እኚሁ ምሁር፡፡

የታሪክ ተመራማሪው እንደሚሉት በደርግ እጅ የተገደሉት አቡነ ቴዎፍሎስ የጀመሯቸው የተቋማዊ አሰራር ውጥኖች ቢኖሩም ራስን በነፃነትና በውጤታማነት ለማስተዳደር በሚያስችል ደረጃ ሳይዳብሩ ቀርተዋል፡፡

የተቋማዊ አሰራሩ ድክመት ባልተቀረፈበት በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ለረጅም ዓመታት በመንበሩ ላይ የቆዩት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ከትምህርታቸውና ከውጭ ዓለም ልምዳቸው በመነሳት ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ቢታሰቡም ከበርካታ በመልካም እርምጃ ከሚጠቀሱባቸው ሥራዎቻቸው ባሻገር የተጠበቁትን ያህል የቤተ ክህነቱን ተቋማዊ አሠራርና አሥተዳደር ከመሠረቱ ለመለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል ሲሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራንና የቅርብ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

ፓትርያሪኩ ይላሉ የአዲስ አበባው ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር ‹‹ከመንግሥት ጋር አላቸው የሚባለው የጠበቀ ግንኙነት መንግሥት በበኩሉ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳየት የቤተ ክርስቲያኒቱን ውስጣዊ ጉዳዮች በሙሉ ለራሷ የተወ በመምሰል በቅኝ አዙር አገዛዝ ‹አስተዳዳራዊ ድክመት ወደ አስተዳዳራዊ ቀውስ እንዲሸጋገር መንገዱን አመቻችቷል› በማለት ይደመድማሉ፡፡

ኢህአዴግ መንግሥትና ሃይማኖትም የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳቸው በአንዳቸው ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም በሚል በግልፅ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አስፍሯል፡፡ እናም የዘመነ ኢህአዲጓ ኢትዮጵያ ለሁሉም ሃይማኖቶች ክፍት መሆኗን በቃልም በተግባርም ያሳየች አገር ሆና ነው ላለፉት ሃያ ዓመታት የተጓዘችው፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ ሙሉ በሙሉ ወደ ተግባር ለመተርጎም ግን ገና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም፣ የሃይማኖት ነፃነትን በግልፅ የተቀበለችና መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በሕገ መንግሥቷ ያጸደቀች አገር ግን አለችን፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ላይ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ቢገልፅም አልፎ አልፎ በተግባር እየታየ ያለው እውነታ ግን በተቃራኒው እንደሆነ ታዛቢዎችና በርካታ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናት ያደረጉ የምሁራን የጥናት ወረቀቶች የሚጠቁሙት፡፡

በሕገ መንግስት ደረጃ ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ ናቸው አንዱ በአንዱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አይገቡም ቢባልም፤ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተመለከተ ግን የኢህአዴግ መንግሥት ትናትናም ሆነ ዛሬ ነፃ ነኝ የሚልበት ድፍረትና ወኔ  ይኖረዋል ብዬ ለማሰብ ግን ፈፅሜ አልደፍርም፡፡ ለዚህም ሙግቴ አንዳንድ አሳማኝ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኢህአዴግ በሕገ መንግሥቱ ‹‹ኢትዮጵያ ለሁሉም ሃይማኖቶች እኩል ናት፣ የመንግሥት ሃይማኖት የሚባል ነገር የለም፣ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡›› ቢልም ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት ወደ ቤተ ክህነቱ ተቋም በድፍረት ዘልቆ በመግባት ያለፈለገውን አውርዶ ያሻውን ለማስቀምጥ የሄደበት መንገድ በወረቀት ላይ ከደነገገው ሕግ ጋር የሚፃረር እንደሆነ ተደጋግሞ የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡

እናም አሁንም ድረስ ለእኔና እኔን ለሚመስሉ ለበርካታዎች ቤተ መንግሥቱና ቤተ ክህነቱ ተለያይተዋል የሚባልበት መሰመሩ የቱ ላይ እንደሆነ በግልጽ ለመጠቆም እየተቸገረን እዚህ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

የኢህአዴግ መንግሥት ‹‹ህመምተኛ ነኝ፣ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመምራት አልችልም፣ በገዛ ፈቃዴ ሥልጣኔን ለቅቄያለሁ…፡፡›› ብለዋል በሚል ሰበብ ከመንበራቸው እንዲሰደዱ የተደረጉት አቡነ መርቆሪዮስ በሂደት ይኸው እስከ ዛሬይቱ ቀን ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ ትልቅ የታሪክ ስብራትና ጠባሳ የሆነ አሳፋሪ ክስተትን ጥሎ አልፏል፡፡

ይህ ክስተት የወለደው መለያየትና መከፋፈልም የሃይማኖት አባቶችን በአብዛኛው የጥላቻ፣ የጠላትነትና የጽንፈኝነት የፍረጃ ፖለቲካ በሚንጠው የአገራችን ፖለቲካ ጎራ አሰልፎ ከቃላት ጦርነት ባለፈ በግልፅ ፖለቲካዊ አቋም እንዲያራምዱ ትልቅ በርን ከፈተ፡፡

ሰሞኑን በተለያዩ መረቦችና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ተለቀው ያየናቸው አንድ በአሜሪካ የሚገኙ የሃይማኖት አባት፣ ‹‹በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ስርዓት፣ ፍትህ፣ የሕግ የበላይነትና ብልጽግና መስፈን አማራጩ መንገድ ጦርነት ነው፣ ሌላ የወንድማማቾች እልቂት፣ ሌላ የአንድ እናት ማኅፀን ልጆች ዳግማዊ ፍጅት ነው፡፡›› ብለው ዱር ቤቴ ካሉ ነፍጥ አንጋች ወገኖቻችንን ጋር በረሃ ድረስ ወርደው የተነሱት ፎቶ የሃይማኖት መሪዎቻችን ላሉበት የአቋም መዋዠቅና ኢ-መንፈሳዊ አካሄድ ትልቅ መሳያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለምሕረትና ለእርቅ ይቆማሉ የምንላቸው አባቶቻችን አድራሻቸው የጦር ግንባር፣ የእልቂት አውድማ ከሆነ እንግዲህ ምን እንላለን!?

ለእውነትና ለፍትህ ጠበቃ ይሆናሉ የምንላቸው አባቶች እርሰ በርሳቸው ተለያይተውና ተከፋፍለው በቃላት ጦርነት የሚሞሻለቁ ከሆነ ፍፃሜያቸው ምንድን ነው!?

የምሕረትና የእውነት አደባባይ በተባለች በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት ላይ ሐሰት ነግሶ፣ ጥላቻ ድል ነስቶ የሚወጣ ከሆነ ምን ማለት ይቻለን ይሆን!?

ቤተ ክህነቱ አሁን ላለበት ቀውስ ተጠያቂው ማነው፡- ራሱ የቤተ ክህነቱ ተቋምና መሪዎቹ ወይስ…?

ዛሬ ቤተ ክርስቲያኒቱ ላለችበት ዘርፈ ብዙ አስተዳዳራዊ ቀውሶች፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ ጎሰኝነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት፣ የመንፈሳዊነት ሕይወት መጥፋት… ወዘተ ተጠያቂው ማነው? ይህ ጽሑፌ ቤተ ክርስቲያኒቱንና የሚመሯትን አባቶች ክብርና ልእልና ዝቅ ለማድረግ ያለመ አድርገው እንዳያዩብኝ አባቶችን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተከታዮችንም ጭምር በትህትና ልገልጽላቸው እወዳለሁ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በቅንነት መንፈስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባሉባት ችግሮች ዙሪያ በቅንነትና በግልፅ ለመወያየት መድረክ ለመክፈት ነው፡፡ በዚህም ከትናንት ታሪካዊ ስህተቶቻችንና ውድቀቶቻችን ተምረን በጋራ ለመፍትሔው ለመመካር እንጂ የማንንም ሰብአዊ ክብርና ማንነት ለመንካት ብዬ አይደለም ይህን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡

ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስመለስ የቤተ ክህነቱ ተቋም አሁን ላለበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዋናው መንስኤ ራሱ ነው፡፡ መፍትሔውም የሚመነጨው ከራሱ ከቤተ ክህነቱ ተቋምና መሪዎቹ እንደሆነ አጥብቄ አምናለሁ፡፡ እስቲ በቅርብ ዘመን ቤተ ክህነቱና መሪዎች የተፈተኑበትን የታሪክ አጋጣሚዎች ከቅርብ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ በመነሳት ለማሳየት ልሞክር፡፡

ቤተ ክህነቱ የራሱን መንፈሳዊ ክብር፣ ኃይል፣ ሥልጣንና ልእልና በመጠበቅ ረገድ ጉልበቴን ያለበትን በርካታ አጋጣሚዎችን እኔና ትውልዴ በተደጋጋሚ ለመታዘብ የቻልንባቸው ወቅቶች ትናንትና ነበሩ፤ ዛሬም ተደቅነውብን አሉ፡፡

የቤተ ክህነቱ ተቋም የሚመሩ አባቶች ይላሉ እውቁ ምሁርና ጸሐፊ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ክህደት ቁልቁለት በሚለው መጽሐፋቸው፡-«ሥጋቸውንየበደሉ፤ ለነፍሳቸውያደሩ» ናቸው ተብሎ ነው በብዙዎቻችን ምእመናን ዘንድ የሚታመነው፡፡የሃይማኖትመሪዎችለጽድቅማለትለእውነትእንዲሁምለፍትሕናለእኩልነትየቆሙናቸውተብሎይታመናል፡፡ ለሀብትናለሥልጣንግድስለሌላቸውከዚህዓለምጣጣውጭናቸውም ተብለው ነው የሚቆጠሩት፡፡

የሃይማኖት መሪዎች ለፍትህ፣ ለስው ልጆች ነፃነትና እኩልነትም ድምፃቸውን የሚያሰሙ የእውነት ጠበቃዎች ናቸው፡፡ ልዩ ክብር በሚያሰጣቸው በመንፈሳዊ ሰብእናቸውና ሥልጣናቸው የተነሣም በእውነትና በፈትህ ተቃራኒ የሚቆሙ መንግስታትን፣ መሪዎችንና ክፉዎችን ሁሉ የመገሰጽና ፊት ለፊት የመቃወም መለኮታዊ ሥልጣን ከላይ ከአርያም የተቸራቸው እንደሆኑ ነው በአብዛኛው ምእመኖቻቸው ዘንድ የሚታሰበው፣ የሚታመነውም፡፡››

ይሁን እንጂ በቤተ ክህነቱ ተቋምና ቤተ ክህነቱን በሚመሩት አባቶች ዙሪያ በእኔ እና በትውልዴ ዘመን እንኳን የታዘብነው እውነታ ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ነበር ወይንም ነው፡፡ ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪ የነበሩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ሲያግዝና በግፍ ሲያስገድል ድርጊቱን በመቃወም ስለ እውነትና ፍትህ ድምፃቸውን ያሰሙ አባቶች እንደነበሩን አልሰማንም፡፡

እንደውም በተቃራኒው አሁን አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ስለ ቅዱስነታቸው ከመንበራቸው መወገድና መገደል ‹‹የክብር ፊርማቸውን በማኖር ሙሉ ስምምነታቸውን የገለጹ የሲኖዶሱ አባላት አባቶች እንደነበሩ ነው፡፡››

የግድያ እርምጃው ማንንም ከማንም ያለየበት ደርግ በእግዚአብሔር የለሽ አቋሙ ትውልዱን በኮሚኒሰት ማኒፌስቶ ጸበል እያጠመቀ ከሃዲ ሲያደርገውና አብያተ ክርስቲያናትም እንዲዘጉ ሲያደርግ፣ የሃይማኖት ሰባኪያን ወደ ወህኒ ሲወረወሩና ሲረሸኑ ትንፍሽ ያለ አባት ነበር እንዴ!?

በሀገሪቱ የሺህ ዘመን ታሪክ የደመቀ አሻራ የነበራት ቤተ ክርስቲያን ሀገሪቱ በጥፋት ገደል ጫፍ ላይ ቆማ በነበረችበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ድምፃቸው ያለመሰማቱ ጉዳይ ምክንያቱ ምን እንደነበር አባቶቻችን አልነገሩንም፤ እኛም ደፍረን አልጠየቅንም፡፡

በተቃራኒው አባቶቻችን በዘመኑ የፖሊቲካ መሪዎች ጋር እጅና ጓንት በመሆን ከወንጌል እውነት ተቃራኒ ለፍትህ፣ ለእውነት፣ በወንድማማቾች መካከል ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያሰማሉ ሲባል ድምፃቸውን አጥፍተው በፍርሃት ድባብ አፋቸው ተሸብቦ ያን የመከራ ዘመን ከሕዝባቸው ጋር ለመቆም አልደፈሩም፡፡

አባቶቻችን የግፍንና የጭቆናን ቀምበር ለመስበር ሕዝቡን ከጎናቸው አሰልፈው ግንባር ቀደም በመሆን ለእርቅ፣ ለፍትህ እና ለሰላም መቆም አለመቻላቸውን ትላንትናም ሆነ ዛሬ አይተናል፣ ታዝበናል፡፡

የአንድ እናት ማኅፀን ልጆች እርስ በርሳቸው ሲተራረዱ፣ በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር የራሺያ የተውሶ አብዮት ምድሪቱ በደም አበላ ተመትታ አኬል ዳማ ስትሆን፣ ወንድማማቾች በርዕዮተ ዓለም ልዩነት አንጃ ፈጥረውና እርስ በርሳቸው ተቧድነው ሲተላለቁ መንግሥትን ተው ያለ፣ ወጣቶቹንስ ከልባቸው እንዲሆኑ የመከረና የዘከረ፣ ስለ ሰላምና እርቅ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያሰማ የሃይማኖት መሪ ነበር እንዴ!?

ይህን የዘመኑን አሰቃቂ ክስተትና የሃይማኖት አባቶች ዝምታን የመረጡበትን እንቆቅልሽ ‹‹ያለመቻቻል ፖለቲካ ሰማዕትነት፡- መቼም እንዳይደገም›› በሚል ሦስት የአገራችን ምሁራን ባቀረቡት የጥናት መጽሔት ላይ የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ ‹‹ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ፡- ታሪካዊ ይዘትና አንድምታ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ወረቀታቸው፡-

‹‹በዘመነ ቀይ ሽብር አገሪቷ አስፈሪ የሆነ የሞት መልአክ ባንዣበባት ወቅት ካህናቱና የሃይማኖት መሪዎች እንደ ጥንቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል ታቦት ተሸክመውና መስቀል ይዘው በመውጣት ስለ ሰላምና ስለ እርቅ ሊሰብኩ ቀርቶ፣ ለራሳቸው ፈርተው ተሸሽገው ነበር፡፡›› በማለት ትዘብታቸውን በመግለፅ በወቅቱ የነበሩትንና አሁንም ድረስ በሕይወት ያሉትን አንጋፋ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶች የዛን ቀውጢ ጊዜ የት እንደነበሩ የጠየቁት፡፡

በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት የሰው ደም በከንቱ ሲፈስ፣ ምርጫ 97ትንተከትሎ እንዲያ አገሪቱ ስትታመስ፣ ሮጠው ያልጠገቡ ሕጻናት በአልሞ ተኳሾች ግንባራቸው በጠራራ ጸሐይ እየተመቱ ሲወድቁ፣ የኢትዮጵያውያን ምስኪን ራሄሎች/እናቶች ዋይታና ፣ ኤሎሄታ፣ የፍርድ ያለህ፣ እያሉ እንባቸውን ወደ ጸባዖት ሲረጩ፣ ስለ ሰላም፣ እርቅና እውነት ይቆሙ ዘንድ የተገባቸው አባቶቻችን ለመሆኑ በዛች ቀውጢ ሰዓት ድምፃቸው ምነዋ አልተሰማ?!

ዛሬ ስለ ፍትህ፣ እውነትና ሰላም ይቆማሉ የምንላቸው አባቶቻችን በተቃራኒው መቆማቸውን ስናይ እኛ መንፈሳዊ ልጆቻቸው በእፍረት እንሸማቀቃለን፡፡ ከዛም አልፎ ዛሬ በግልጽ እያየንና እየሰማን ያለነው የሞራል ውድቀቱ፣ ዘረኝነቱ፣ ሙስናው፣ የመንፈሳዊ ሕይወት መጣቱ ጉዳይ ሌላ ትልቅ ቀውስ ሆነ ብቅ ብሏል፡፡ እናም የነገ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ክብርስ ምን ሊሆን ይችላል በሚል በዋይታና በለቅሶ እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ዓይኖቻችንን ወደ አርያም ለማንሳት እንገደዳለን፡፡

አሁን በመሪነት ያሉ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች በከፍተኛ የአመራር ስነ ምግባር ብልሹነት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ መናገር እንደ ዜና እንኳን የሚቆጠርበትን ደረጃ ካለፍን ሰንብቷል፡፡ በእነዚህ የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ነን በሚሉ ሰዎች እየተፈጸመ ያለው ድርጊት የእነርሱን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የማኅበረሰባችንን የሞራል ድቀት፣ የአመራር ዝቅጠትና ራእይ አልባነት የሚያረጋግጥልን ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹን የሃይማኖት መሪዎች ማጋለጥ በአንዳንዶች የዋኻን ዘንድ የሃይማኖቱን ወይም ተቋማቱን እንደ ማዋረድ ተደርጎ ይሰበካል ወይም ይቆጠራል፡፡

በሌላ በኩል ይህን አመለካከት ተቋቁሜ ድርጊቱ እንዲታረም እታገላለሁ የሚል የሃይማኖት አባትም ሆነ ምእመን ቢገኝ እንኳን አቤቱታውን የሚያሰማበት መድረክም ሆነ አካል የለም፡፡ ‹‹የሃይማኖት መሪ ቢያጠፋ እንኳን ልንጸልይለት እንጂ እንደ ሥጋውያን ልንጠይቀው አይገባም፡፡›› የሚል እውነት ቀመስ የሐሰት ምሽጋቸውን ይቆፍራሉ፣ ያስቆፍራሉ፡፡

ታዲያ ይህን መሰል ማኅበረሰባዊ ክብራቸውን የሕገ ወጥነትና የኢ-ሞራላዊነት መደበቂያ ያደረጉ የሃይማኖት አባትና መሪዎች ነን የሚሉ እስከ መቼ እንዲህ ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ድቀት፣ ቀውስና ዝቅጠት ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲየን በአንፃሩ ደግሞ ለትንሳኤዋ የሚተጉ እንደ ንጉሥ ዳዊት ባለ መንፈሳዊነት ‹‹የቤትህ ቅናት በላኝ›› በሚል መንፈሳዊ እልኽና ቁጭት የሚተጉ አባቶችና መሪዎች እንዳሉም አልዘነጋም፡፡

እንደ ነቢዩ ኤልያስም ስለ ቅዱስ መቅደሱና ስለ አምልኮተ እግዚአብሔር በፍፁም ነፍሳቸው የሚቀኑ፣ ከበዓል ነቢያትና በሃይማኖት ካባ ስር ተሸሽገው ካሉ አስመሳዮች ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ስለ እውነትና ፍትህ የሚከራከሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ትላንትና እንደነበሩና ዛሬም እንዳሉ ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡ እንደ ነቢዩ ኤርምያስም እንባቸውን እያፈሰሱ ‹‹አቤቱ እባክህ የሆነብንን አስብ…!›› የሚሉ አባቶችና ምእመናን በመቅደሱ አደባባይና በጓዳ ውስጥ ዛሬም እንዳልጠፉ አምናለሁ፡፡

የተነሳሁበትን የቤተ ክህነቱን ጉዳይ በአንድ ክፍል ለመጨረስ የሚቻል አልሆነም፡፡ ስለዚህም በቀጣይ ጽሑፌ በተለይ በኢትዮጵያውና በአሜሪካው ሲኖዶስ መካከል ሰላማዊ ድርድሩ ወዴየት ያመራ ይሆን፣ የቀድሞው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ በሚሉና በፓትርያሪክ ምርጫ ዙሪያ የሚነሱትን አስተያየቶችና ውዝግቦች፣ የመንግስትን ስውር እጅና ጫና በተመለከተ በቤተ ክርስቲያኒቱ የቅርብ ታሪክ ላይ በመንተራስ ለመተንተን የሚሞክረውን ጽሑፌን በቀጣይ ሳምንት ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ሰላም! ሻሎም!

Advertisements

Posted on January 3, 2013, in Human Right, News, Politics and tagged , , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s