የሌለ ዲሞክራሲ ይሰጣልን?

ከይኸነው አንተሁነኝ
የካቲት 4 2013

ከታላቋ ሩሲያ መከፋፈልና ከኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም መንኮታኮት በሗላ ጥቂት የማይባሉ ሀገሮች እና ለለውጥ እንታገላለን ሲሉ የነበሩ ድርጅቶች መመሪያችን ነው እያሉ ሲያመልኩት የኖሩትን የሶሻሊዝም አይዲዮሎጂ፤ የተናገሩት ሳያቅራቸው የጻፉት ሳያሳፍራቸው ባንዲት ጀንበር እርግፍ አድርገው፤ ጥቅም እስከተገኘ ድረስ በሉ የተባሉትን ለማለት ሁኑ የተባሉትን ለመሆን ተሯሯጡ። እጃችሁ ከምን እያሉ ሲያባብሏቸው የነበሩትን የትላንት ወዳጅ መከታ ሀገሮችን ረሱ። ሌላው ቀርቶ በየድርጅቶቻቸው ውስጥ ይሰጥ በነበረው ርዕዮት ያጠመቋቸውን የራሳቸውን አባላት ልጆቻቸውን ጭምር ክደው እንደ እስስት መልካቸውን ቀየሩ። እጅግ የከፉት እንደ ወያኔ ያሉት የጎጥ ድርጅቶች ደግሞ ስለ ለውጡ እንዴትነት የጠየቋቸውን የራሳቸውን ጓዶች ሳይቀር ቅርጥፍ አድርገው እየበሉ አሁን ላሉበት ደረጃ ደረሱ።

በአጥቢነት ላይ በራሪነትን ደርባ እንደለበሰችው እንደ ሌሊት ወፍ በእውነተኛው ኮሚኒስት ማንነታቸው ላይ ደርበው ግን ዲሞክራሲያዊነት መርሃችን ነው የሚሉት ወያኔዎች፤ ምንም እንኳ ጥቂት የማይባሉ የዲሞክረሲ መርሆችን ፖሊሲዎቻቸውን በከተቡበት ወረቀት ላይ ለማስቀመጥ ቢሞክሩም፤ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በደርዘን ለሚቆጠሩ ጊዜያት ኮሚንስታዊ አምባገነንነታቸውና አፋኝነታቸው በግልጽ ሲጋለጥባቸው እንደቆየና አሁንም እየተጋለጠ እንደሆነ የማይታበል ሀቅ ነው።

በደርግ የአምባገነን አገዛዝ ተረግጦ ሲገዛ ለነበረው ሕዝባችን ዲሞክራሲን ይዘንልህ መጣን ያሉት ወያኔዎች፤ በወያኔ መንደር በተለያዩ ቦታዎችና በተደጋጋሚ ከተነሱት የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ጋር አብሮ ለመጓዝ ወይም በተቃራኒው ለመንቀሳቀስ ሕዝባችንን ያልሆነውንና የማይፈልገውን እንዲሆን በጉልበት አስገድደዋል። ሕዝባችን ወዶ ያደረገውን ፈልጎ የፈጸመውን ድርጊት በግፊትና በተጽእኖ እንዳደረገው በመስበክ የእኛ እናውቅልሃለን አፈናቸውን ፈጽመዋል። በጥቅሉ በዲሞክራሲ ስም ኢድሞክራሲያዊነታቸውን አሳይተዋል።

በአንዲት ሀገር የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ የዜጎች መሰረታዊ ብቶች የሆኑት የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ መረጃ የማግኘት እና የሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚጠበቅ ነው። እነዚህን ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው የሆኑትን እንእስቃሴዎች በማድረጋቸው ዜጎች ሊሳቀቁና ሊዋከቡ አይገባም። ይልቅስ ለዝግጅታቻቸውና ለእንቅስቃሴዎቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ከማሟላት ጀምሮ በእንቅስቀሴው ወቅት ደረጃውን የጠበቀ ጥበቃ ማድረግ ከሀገሪቱ መንግስት ይጠበቃል። ይህ እንግዲህ ለሚያስተዳድሯቸው ሕዝቦች በእውነት የመንግስትነትን ስራ እየሰሩ ላሉ መንግስታት ነው። የኛው ሀገር ወያኔ ግን በዲሞክራሲ ስም አፈናን ግፍን አሰፋፍቷል። በመናገርና መጻፍ መብት ስም የወያኔን ፖሊሲዎችና አጠቃላይ አሰራሩን ተችተው የተናገሩትንና የጻፉትን አስሯል አሳዷል ገድሏል። መረጃን ለሕዝብ በማድረስ ስምም መድረስና መሰማት ያለባቸውን መረጃዎች ሳይሆን የወያኔን ፐሮፖጋንዳ በሁሉም ሬዲዮዎችና ቴሌቪዥኖች ሲሰብክ ከርሟል።

በወያኔ አሉታዊ ተግባር ወያኔ ያጸደቃቸውንና በጽሁፍ ላይ ብቻ የሚገኙትን መብቶች በመጥቀስ ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት ብርቅዬ ዜጎቻችን፤ በስደት ዓለም ጠንክረው በመንቀሳቀስ በራሳቸው ግለሰባዊ ወጭ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሰራጫዎችን ከፍተው የወያኔን ጠባብነት፣ ከፋፋይነትና ሀገር አጥፊነት በማጋለጥ ላይ ቢሆኑም እጀ ረዥሙ ወያኔ ግን ውቅያኖስ ተሻጋሪ ሴራውን ልሳኑ በሆነው ትግራይ ኦን ላይን በኩል እየሰነዘረ ይገኛል።

በውጭ የሚገኙት ወገኖቻችን የመናገር መብታቸውን ተጠቅመው ካቋቋሟቸው ማሰራጫዎች አንዱ በሆነው ኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን አማካኝነት ድምጽ ለሌለው ሕዝባችን ድምጽ ለመሆን እየሰሩ ባሉበት በዚህ ወቅት፤ ወያኔ ግን ሃሳብን በሃሳብ በመታገል ፋንታ በተካነው የመከፋፈልና እርስ በርስ የማጋጨት ጥበቡ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ክርክር የማያውቀውን የትግራይ ሕዝብ ከተቀረው የሀገሪቱ ሕዝብ እና ከብቸኛው የኢትዮጵያ እውነተኛ ድምጽ ኢሳት ጋር ለማጋጨትና ያልተከለሰ እውነተኛ መረጃ እንዳያገኝ ለማድረግ በርትቶ እየሰራ ይገኛል። ወያኔ በትግራይ ሕዝብ ለመነገድ ትግራይን የበላይ ሌሎችን ብሕሮች ተከታይ አድርጎ ለማሳየት ሞክሯል። ወያኔ ሌላ የሚለው ብሔርም በማንነቱ እንዲያፍር፣ በሃይማኖቱ ለዘብተኛ እንዲሆንና ብሔራዊ ስሜቱም እንዲቀንስ ለማድረግ ጥሯል። የተዛባ፣ ያልተጠናና መሰረት የሌለው የፖለቲካ አካሄድን በመከተልና ዳር የወጣ ጠባብ ዘረኝነትን በማራመድ ወደፊት መቋጫ የሌለው የእርስ በርስ ትርምስ እንዲፈነዳ በርትቶ እየሰራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ወያኔዎች ምንም እንኳ ከትግራይ ክልል የወጡም ቢሆኑ አገዛዙን የተቆናጠቱት ጥቂት ጉጅሌዎች ብቻ በሃብት፣ በስልጣን፣ በትምህርትና በመሳሰሉት ይጠቀሙ እንጅ ሂዎት ለተቀረው የትግራይ ሕዝብ ግን እንደተቀረው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽህ ቢታለብ ያው በገሌ መሆኑን የትግራይ ሕዝብ አሳምሮ አውቃል።

ይህን ያልተረዳው ወይም ሆን ብሎ ለመረዳት ያልፈለገው ወያኔ ግን አሁንም የጠባብ ዘረኝነት ድሪቶውን በትግራይ ሕዝብ ላይ ለመጫንና ከውጤቱ ተጠቃሚ ለመሆን እየሞከረ ይገኛል። የትግራይ ሕዝብ ግን እየደረሰበት ያለው ግፍና መከራው በተነሳለት እንጅ እውነተኛው ወገኑ ማን እንደሆነ ለማወቅስ በትግራይ ሕዝብ ስም እንደሚቀልደው እንደ ትግራይ ኦን ላይን ያለ አስተማሪ ባላስፈለገውም ነበር።

አውነት በተነገረ ቁጥር ማስፈራራት የሚቀናው ሚስጥራዊው ጎጠኛ ድርጅት ወያኔ የሚስጥር ጓዳው ሲበረበር ቢያብድ የሚያስገርም አይሆንም። ምክንያቱም እጅግ ሚስጥራዊ ከመሆኑ የተነሳ ዓለም የሚያውቀው መልኩና እውነተኛው ሚስጥራዊ ማንነቱ እጅግ የተለያዩ ነቸውና። በዚህ የተነሳም ይህ ሳምንት እውነተኛ ግለሰቦችና ኢሳትን የመሰሉ የዜና ድርጅቶች እውነትን በመናገረቸው ሚስጥርን በማጋለጣቸው ብቻ ማስፈራሪያ እየተላከላቸውና እየተጻፈባቸው ያሉት። ወያኔዎችም በዚህ መልኩ የዲሞክራሲ መብቶቻችንን የመርገጥና የማፈን እርምጃዎችን ቢቀጥሉም ትግላችን ግን እጅግ በበረታና በተጠናከረ መልኩ ቀጠለ እንጅ አላቆመም።

ecadf.com

Advertisements

Posted on February 4, 2013, in News, Politics and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s