የኢትዮጵያዊያን ትግል

(ከአንዱ ዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ)

eskemechie

June 25, 2013 07:40 am By  Leave a Comment

ክፍል አንድ

የመድረክ የአደባባይ ውይይትን በመንተራስ

የአንድነት ፓርቲ ግምገማዉንና የመድረክ አመራር መልሱን በአደባባይ ማቅረባቸው ታላቅ በር ከፋች ጥረት ነው። አንድነት መድረክን ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን አመራር አካላትም ገምግሞ ለኢትዮጵያዊያን ማሳየቱ፤ ብስለቱንና ጥንካሬውን አመልካች ነው። ከመድረክ በኩል የተሠጠውም መልስ፤ በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ መውጣቱ የሚያኮራ ነው። እዚህ ላይ አንዱም ሆነ ሁለቱ ትክክል ናቸው ወይንም ስህተተኞች ናቸው ማለቴ አይደለም። ጥረታቸው የሚያኮራ መሆኑን ለመጠቆም ነው። በዴሞክራሲያዊ ማዕከልነት ስምና በፓርቲ አባልነት ግዴታ ማነቆ ልሳናቸው ሳይዘጋ የተጻጻፉበት ምልልስ፤ ትልቅ ትምህርት ለሁላችን ሠጥቷል። እስከዛሬ ያልተለመደው ግልፅነት በሩ ተከፈተለት። ራሳችንን መገምገም ራሳችንን ዝቅ እንደማድረግ ስለሚወሰድና ይኼን ማድረግ እንደተቸናፊነት ስለሚወሰድ፤ ከትናንት ትምህርት የመውሰዱ ሂደት በሩ ዝግ ነበር። አሁን በሩ ተከፈተ። ሀቅ ይረዳል እንጂ ማንንም አይጎዳም። ይኼ ግን ባህላችን አልነበረም። ጥሩ ነገር ስናይ ደግሞ፤ ማንም ይሥራው ማንም ይበል ማለት ተገቢ ነው።

ጉዳዩ የሁላችን ነው

የተወያዩባቸው ጉዳዮች የግላቸው ሳይሆኑ፤ ሁላችን ኢትዮጵያዊያንን የሚነኩና እኩል እንደነሱ ልንወያይባቸው የሚገባ ነው። ትኩረቱ እከሌ እንዲህ አለ፤ ሌላው ደግሞ ይኼን መለሰለት ለማለት ሳይሆን፤ ባደረጉት ምልልስ የተነሱት ነጥቦች በሁላችንም ዘንድ መልስ ፈላጊ በመሆናቸው፤ በየበኩላችን እንድንወያይበት ይገፋናልና የበኩሌን ለመለገስ ነው። አሁንም እንደገና፤ ግልፅ ውይይት ማድረግ በማንኛውም ወቅት የጥንካሬ፣ በተጨማሪም ራስን ደግሞ ደጋግሞ በየደረሱበት ደረጃ መመርመር፤ ለትግሉ ውጤት ያለንን ቁርጠኝነት መለኪያ መሣሪያዎች ናቸው።

ጉዳዩ እንዲህ ነው። መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረ የፖለቲካ ድርጅት ነው። የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ተንትነው አንድ መፍትሔ በማቅረብ፤ የርዕዩተ ዓለም አመለካከታቸው አንድ የሆነ አባላት ያሉበት ድርጅት ነው። በሌላው በኩል በአካባቢ ወገኖቻቸውን በማሰባሰብ የተዋቀሩ ድርጅቶች አሉ። እኒህ ድርጅቶች የአካባቢያቸው ተቆርቋሪ በመሆን አጀንዳቸውን ያማከሉ ድርጅቶች ናቸው። መድረክን ለመፍጠር በሁለቱ ወገን ያሉ ክፍሎች ወይይት አድርገው፤ በኢትዮጵያ በነበረው ሀቅ ተገደው፤ የተወሰነ ስምምነት ላይ ደረሱ። ይህ መድረክ ወደፊት ምን ሊሆን እንደሚችል ያኔ በደንብ ያጤኑት ላለመሆኑ፤ የአንድነት ፓርቲ ግምገማ ግልፅ አድርጎልናል። አሁን ዕድገታቸውን አስመልክቶ ወደፊት ሲሉ፤ በወቅቱ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አስረው ያዟቸውና፤ ከፊታችን ለተደቀነው ውይይት በቁ። ታዲያ ከዚህ ምን እንማራለን?

እውነት ስትፈተን

እያንዳንዳችን መብትና ግዴታችን የሚመነጨው ከኢትዮጵያዊነታችን ነው። መብታችን ሊከበር፣ ኃላፊነታችን ሊጠየቅ የሚገባው፤ በኢትዮጵያዊነታችን ነው። ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በምንኖርባት ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያዊነት የተለዬ መብትና ግዴታ የለንም። አማራ ሆኜ በአማራነቴ መብቴና ግዴታዬ፤ በኢትዮጵያ፤ እንደ ትግሬ ወይንም እንደ ኦሮሞ ወይንም እንደ ሶማሌ ሳይሆን እንደ አማራ ይከበርልኝ ብል፤ የምናገረውን የማላውቅ መብት ፈላጊ እሆናለሁ። አማራ መሆኔ የኔ ጉዳይ ነው። ከአማራና ከኦሮሞ መወለዴ የራሴ ቤተሰብ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ስኖር፤ አማራ ወይንም ኦሮሞ፣ ሶማሌ ወይንም አፋር፣ ትግሬ ወይንም ወላይታ መሆን የለብኝም። ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኔ ነው መለኪያው። ከአንዱ ወይንም ከአንዱ በላይ ከሆኑ ቤተሰብ መወለዱ፤ የግለሰቡ የቤተሰብ ትስስር ጉዳይ ነው። ይህ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብቱ ሊጨምርለት ወይንም ሊያስቀርበት አይችልም። ታዲያ ምኑ ላይ ነው ችግሩ? ችግሩ የተከሰተው፤ ከዚህ ወይንም ከዚያ በመወለዴ የቀረብኝ ወይንም የደረሰብኝ ወይንም የሚቀርብኝ ወይንም የሚደርስብኝ ጥቅም ወይንም በደል ነው። ይህ ያለአንዳች ጥያቄ በሀገራችን የተከሰተ ችግር ነው። መለያየት የሚመጣው መፍትሔ ሲታሰብ ነው። መፍትሔው ደግሞ፤ ላንድ ወቅት ወይንም ላንድ ክፍል የሚሰራ ሳይሆን፤ ሁሌም ለሁሉም የሚሠራ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ፤ በሕገ-መንግሥቱ፣ በመንግሥቱና በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሊከበርና ሊጠበቅ የሚገባው መሆኑ ነው። በዚህ ላይ በአንድነት መነሳት አለብን። በውጭ ሀገር በየተሰደድንበት ቦታ፤ መብታችን በሀገሩ ካሉ ነዋሪዎች በአንዲት ጠብታ ሳታንስ እንዲከበርልን ሽንጣችንን ገትረን እንቆማለን። የሀገሩን ዜግነት ተቀበልንም አልተቀበልንም ልዩነት አናይበትም። ታዲያ ኢትዮጵያ ላይ ምን ልዩነት ተፈጠረ? የሀገሩ ዜጋ በሙሉ እኩልነታቸው የሚመዘገበው፤ የሀገሩ ዜጎች በመሆናቸው ብቻ ነው።

የትግላችን ግብ

ኢትዮጵያዊያን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር የምናደርገው ትግል፤ ይኼን በጉልበቱ በሥልጣን ላይ ያለን ቡድን ስሙን ስለጠላን ለማስወገድና ሌላ ስም ያለው በቦታው ለመተካት አይደለም። መሠረታዊ የትግሉ መነሻው የዚህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍናውና የአስተዳደር መመሪያው ናቸው። እኒህ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያዎቹ በሀገራችን ተዘርፍጠው መቀመጥ ቀርቶ ባንዣበቡበት ሁኔታ፤ ወደፊት መሄድ የሚባል ጉዳይ የለም። የትግል እሽክርክሪቱ ተወግዶ ወደፊት እንድንሄድ ከተፈለገ፤ ግልፅ የሆነ ውይይት ማድረግ አለብን። በአሥራ ዘጠኝ መቶ ስድሳዎቹ የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋናው የትግል መስመሩ፤ በገዢዎችና በተገዢዎች መካከል የነበረው ቅራኔ ነበር። በዚህ የተጠቃለሉት የዴሞክራሲያ ጥያቄዎች፤ መሬት ላራሹ፣ የትምህርት ዕድል ለብዙኀኑ፤ ሕክምና ለገጠሬው፣ ኃላፊነት ለፓርላማው፣ የሴቶች እኩልነት፣ በወቅቱ ትክክለኛ ትኩረት ያልተደረገበትና የዘመኑ የሶቪየት ኅብረት ሶሺያሊዝምን መስመር ያንፀባረቀው የብሔሮች እኩልነት ነበሩ ከሞላ ጎደል ሰንደቆቻቸው። በመደብ ትግሉ ጠንካራ አቋም ከነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተገንጥለው፤“በኢትዮጵያ የብሔሮች ነፃ መውጣት ነው ቅድሚያ ያለው” ብለው የተነሱ ጥቂት ቡድኖች ነበሩ። በዚህ የተመሩ የብሔር ነፃ አውጪ ቡድኖች በሀገራችን ግራ ቀኙን ተሯሯጡበት። ተጨባጭ የነበረው የአድልዖና የጭቆና ክስተት፤ ለትንንሽ መንግሥታት መፍጠሪያ መንገዱን ከፈተ። ለነበረው ሀቅ አንድ ብቻ መፍትሔ ሳይሆን ብዙ መንገዶች ቀረቡ። አንድ ሀገር የሚለው ጉዳይ በአንዳንዶች ዘንድ ተቀባይነት አጣ። በዕርግጥ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የፈለገው በሀገራችን ውስጥ የነበረውን የገዢዎችና የተገዢዎች ቅራኔ መፍታት ሲሆን፤ ጥቂቶች ደግሞ የተለዬ መፍትሔ ብለው የያዙት የራሳቸውን ሀገር የመመሥረት አጀንዳ ነበር።

አጀንዳ ያልለወጠ ነፃ አውጪ

ይኼን የመጨረሻውን መንገድ የመረጡት የነፃ አውጪ ግንባሮችን በመመሥረት ጠመጃቸውን አነሱ። በባንዳነት ጣሊያንን በማገልገል የታወቁ የትግራይና የኤርትራ ተወላጆች ልጆች፤ ጠንካራ የሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ መርኀ-ግብር ይዘው፤ ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳቸውን በራሳቸውና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች መመሪያቸው አደረጉ። በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ የረዳው ደግሞ፤ የደርግ ደርጋማ ማንነትና የተከተለው መመሪያ ነበር። ሥልጣን ለብቻው መያዝ ዋናው ዓላማው ያደረገው የመንግሥቱ ኃይለማርያም አረመኔ ደርግ፤ ወጣቶችን በመጨፍጨፍ፤ በእውነትና በሕልሙ ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የፈረጃቸውን በማሳደድና የራሱ ሰው በላ ቡችሎችን በከፍተኛ ቦታ በማስቀመጥ፤ ሀገራችንን ወደ አዘቅት ከተታት። የዚህ ውጤቱ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሀገሪቱን ወለል አድርጎ ከፍቶ ሀገር ለቆ መሽምጠጥ ሆኗል። ታዲያ የብሔሮች ነፃ መውጣትን ያነገበው ይኼ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ትግራይን ነፃ ከማውጣት ይልቅ፤ በተፈጠረለት ቀዳዳ ገብቶ ሀገሪቱን ተቆጣጠረ። አጀንዳውን ሳይለውጥ፤ አሁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ሆኖ አዲስ አበባ ተዘርፍጧል። ባለበት ቦታ ደግሞ የሚሠራው ሀገራችንን መበጣጠስ ነው። ሀገራችንን ሀገር የሚባል ነገር ጠፍቶ፤ የየራሳቸው ብሔር የሚኖራቸው ሕዝቦች ያሉበት ቦታ አድርጓታል። ይህ ነው የትግሬዎች ነፃ አውጪ አጀንዳ። ይኼን ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታገለው። ታዲያ በየአካባቢያቸው የተዳራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች ዓላማቸው ምንድን ነው? የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚከተለውን ዓላማ ማራመድ ነው ወይንስ መለወጥ? ሀገራችንን በጋራ ነፃ አውጥተን ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እኩል የምትሆን ሀገር ማድረግ ነው? ይህ ነው መሠረታዊው የመድረክ ምስቅልቅል።

“አትከፋፍሉን። አንድ ነን።”

አንድነት የፖለቲካ ግኘታ ቋምጦ ነበር ከአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተቧደነው። አሁን ጠዘጠዘው። የግድ ከዚህ መላቀቅ አለበት። በአዲስ አበባ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፤ “አትከፋፍሉን። አንድ ነን።” ነበር ያለው። የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል በሰማያዊ ፓርቲና በመሰሎቹ ወደፊት መጪ ፓርቲዎች እንጂ፤ በነበሩት የነፃ አውጪና የማያፈሩ የቆዩ ፓርቲዎች እጅ አይደለም። የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶችን ከሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶች በዋናነት የሚለያቸው፤ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌሎችን አግላይ መሆናቸው ነው። በነዚህ ድርጅቶች ውስጥ፤ በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ የሀገሪቱ ዜጎች፤ አባል ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት ነው። ከዚህ ተነስተውም፤ እንንቀሳቀስበታለን በሚሉት የራሳቸው ክልል፤ የሀገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችን መንቀሳቀስ በድፍኑ ይቃወማሉ። የርዕዩተ ዓለም ልዩነት ሳይሆን፤ የዚህ አካባቢ ሕጋዊ ተወካዮች እኛ ብቻ ነን ስለሚሉ፤ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ማንኛውንም ዓይነት ስምምነት ለመድረስ፤ በነሱ አካባቢ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለማድረግ ቅድመ-ግዴታ ይሆናል። ይኼን የተቀበለ ሀገር አቀፍ ድርጅት፤ አንድም በነዚህ አካባቢ ያሉትን ደጋፊዎቹ የሀገሪቱ ነዋሪዎች ሸጧል ማለት ነው፤ አለያም የሚያደርገውን የማያውቅ ድርጅት ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅደር፤ በአካባቢ በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶችና በሀገር አቀፍ በተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ቅንጣት ታክል ፍቅር የለም። ግንባርማ ቅዠት ነው። ኢሕአዴግም ውሎ አድሮ ሲበጣጠስ፤ ይኼኑ ያሳየናል።

ውሃ ቢያጥቡት

ሥር የሰደደ ቂም ካለው የትግራይ ታሪክ የተያያዘ መነሻ ያለው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ድርጅት፤*1 ኢትዮጵያን ማፈራረስ ዋና ዓላማው ነው። እንደ ኢትዮጵያዊያ ሳይሆን፤ የተገነጣጠልን ሆነን ራሳችንን እንድንመለከት ነው መርሁ። አንዳንድ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለምን ሀገር አቀፍ የሆነ ድርጅት እንዳልመሠረቱ ወይንም ሀገር አቀፍ ከሆኑ ድርጅቶች እንዳልተቀላቀሉ ሲጠየቁ፤ የሠጡት መልስ ወንዝ አያሻግርም። ዶክተር መራራ መልሳቸው፤ “እኛ ለኦሮሞ ሕዝብ የቆመ ድርጅት ይዘን ካልተገኘን፤ ሕዝቡ ወደ ኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) ይነጉዳል።” ነበር። እንግዲህ የዶክተር መራራ ድርጅት የሚፎካከረው ኦሮሞዎችን ከኦነግ ጋር እንዳይሠለፉ ገንጥሎ፤ በሥሩ ለማድረግ ብቻ ነው። አቶ ገብሩ አሥራትም በበኩላቸው፤ “የትግራይ ሕዝብ የራሱ የሆነ ድርጅት ካላቀረብንለት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብቸኛ ወኪላቸው በመሆን ያጠቃልላቸዋል።” ይላሉ። በዕርግጥ ቃል በቃል አልተጠቀሱም። መልሳቸው ግን ማንነታቸውን በግልፅ ያሳያል። የአቶ ገብሩ አሥራት አረና የሚፎካከረው ትግሬዎችን በሥሩ ለማድረግ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ነው። የዶክተር አረጋዊ በርሄና የአቶ ግደይ ዘርዓፂዮን ታንድም እንዲሁ።

የግለሰብ መብትና የቡድን መብት – በግልፅ ከተነጋገርን

በግለሰብና በቡድን መብቶች ዙሪያ ብዙ ስለተጻፈ እዚህ ላይ መተንተኑ አስፈላጊ አይደለም። እግረ መንገዴን ግን የቡድን የምንለው መብት በግለሰብ መብት ውስጥ ሙሉ በሙሉ የተጠቃለለና በትክክለኛ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ብቻውን መቆም የማይችል መሆኑን ማስታወስ እወዳለሁ። አቶ ገብሩ አሥራት፣ ዶክተር አረጋዊ በርሄና አቶ ግደይ ዘርዓፂዮን ትግሬዎችን ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለመውሰድ ከሆነ የሚታገሉት ለምን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በከለለው በትግራይ ምድር ብቻ ተመዝግበው አይታገሉም? በእውነት ለመናገር፤ ለትግሬዎች ከሀገር አቀፍ በርዕዩተ ዓለም የተመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት ሌላ፤ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የበለጠ አረናና ታንድ ይጠቅማሉ? ይኼ ያጠራጥራል። ይልቁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሲወድቅ፤ ትግሬዎች በደል እንዳይደርስባቸው ቦታ መያዣ የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው። ዶክተር መራራም ሀገራዊ ፍቅር ኖሯቸው ሳይሆን፤ ለሥልጣን ሊያቀርባቸው የሚችለው፤ የአካባቢ የፖለቲካ ድርጅት በመመሥረት ስለሆነ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ዶክተር በየነ ጴጥሮስም የዚሁ አባዜ ተጠቂ ናቸው። ታዲያ ዶክተር መራራም ሆኑ ዶክተር በየነ ለምን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በከለለው የኦሮሚያና የደቡብ ክፍል ተመዝግበው አይታገሉም? ይህ እንግዲህ በግልፅ እንነጋገር ከተባለ ነው። ታዲያ ለኔ፤ በመድረክ ውስጥ የታዬው ድራማ ከዚህ በላይ የተገለፀው ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅደር የሚሳተፍና በሕዝቡ ላይ እምነት ያለው ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቀርቦ ሃሳቡን መግለፅና አሳምኖ ተከታዮችን ማግኘት እንጂ፤ በአንድ የተለዬ አካባቢ ቀርቦ፤ ለዚያ አካባቢ ተከላካይና የዚያ አካባቢ ጠባቂ ለመሆን አያስብም።

የመገንጠል ግብ

መገንዘብ ያለብን፤ በሥልጣን ላይ ያለውን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መጣል ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል ዓላማቸው አድርገው የሚታገሉ የአካባቢ ድርጅቶች እንዳሉ ነው። እነኚህን ለይቶ ማስቀመጥና ከነዚህ ጋር ሊኖር የሚችለውን ግንኙነት ማጥናት ግዴታ ነው። በዕውነት ግን ከነዚህ ጋር ምን ዓይነት ቅርርብ ሊደረግ ይቻላል? ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተነሱ ድርጅቶች ጋር የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ለማስወገድ መሠለፍ፤ የራስን አንገት ለማስቆረጥ፤ ከጎራዴ መዛዡ ጋር መስማማት ነው።

*1  የዶክተር አረጋዊ በርሄን የማስተርስና የዶርትሬት ጽሑፍና መጽሐፋቸውን ይመልከቱ። በአፄ ሚኒሊክ ላይ ያስቀመጡት ውንጀላ በግልፅ ተቀምጧል።


የኢትዮጵያዊያን ትግል – ( ክፍል ሁለት )

“ለየብቻችን ተማክለን እንጂ በአንድነት ተዋሕደን አንኖርም።” የሚለው ቅኝት፤

ከሁሉ በፊት ያለው ጥያቄ፤ ኢትዮጵያዊ ነዎት ወይ? ነው። መልስዎ አዎ ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲሉ፤ ምን ማለትዎ ነው? ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው? እርስዎ ኢትዮጵያዊነትዎን ሲያስቡ፤ ለግል፣ ለራስዎ የሚሰማዎ ምንድን ነው? ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ለማናችንም ቢሆን መነሻ ወለላችን ይህ ነው። ይኼን ስናጤንና አጢነን ለዚህ የምንሠጠው መልስ፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ያለንንና የሚኖረንን ግንኙነት ይወስናል። እናም በአንድነት ለምናደርገው ተግባር፤ ተርጓሚ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ለአንድ ኢትዮጵያዊ፤ ጊዜ የማይቀይረው፣ ሁኔታ የማይለውጠው፣ የግል ጥቅም የማያነቃንቀውና ቦታ የማያርቀው የምንነት አካል ነው። ዜግነቱ ብቻ አይደለም። ከዚያ በላይ ነው። ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በኢትዮጵያዊነቱ የመኖር መብት አለው። ይኼ ደግሞ ሊተገበር የሚችለው፤ አንድ ግለሰብ፤ በኅብረተሰብ የፖለቲካ ተሳትፎው መመዘኛው ኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ሆኖ ሲገኝ ነው። ኢትዮጵያዊ በመሆኑ፤ መብቶቹ ሁሉ ይከበራሉ። አንዱ ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ በማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ብልጫ ወይንም አነስተኛ ድርሻ ሊኖረው አይገባም። የታሪክ አንድነታችን፣ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያበጀልን ያካባቢ ማነቆ፣ ታሪክን በደንብ መረዳት ግዴታችን መሆኑ፤ ኃላፊነታችን፣ የሌሎች ተመክሮና የዚህ ክፍል ማሳረጊያ እነሆ!

የታሪክ አንድነታችን፤

የእንግሊዝ፣ የጣሊያን፣ የቱርክ፣ የግብፅ፣ የሱዳንና የፈረንሳይ ወራሪዎችን በተለያዩ የታሪካችን ወቅቶች የተጋፈጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ፋሽስት ጣሊያን በኛ ላይ ያደረገውን ተደጋጋሚ ጦርነቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ነበር ገትሮ የተቋቋመው። በነዚህ ውጊያዎች ቆራጥ የሆኑ አያቶቻችን፤ ከዘርዓይ ድረስ እስከ አብቹ፣ ከበላይ ዘለቀ እስከ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ከአብረሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም እስከ ጣይቱ ብጡል፣ ከታከለ ወልደ ኃዋሪያት እስከ አዳነ አባ ደፋር በአንድነት አኩሪ ተግባር ፈፅመው አልፈዋል። በኤርትራ በኩል፣ በሱማሌ በኩል፣ በሱዳን በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲመጡብን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተሠልፏል። ሽብሬ ደሳለኝ ለአማራ ወይንም ለኦሮሞ፣ ለትግሬ ወይንም ለወላይታ፣ ለሲዳማ ወይንም ለአኙዋክ ሳትል፤ ለኛ ለሁላችን ለኢትዮጵያዊያን ነፃነት ሕይወቷን የሰጠች ኢትዮጵያዊት ነበረች። ከየትኛው የኢትዮጵያ ክልል ከሚኖሩ ወገኖች መወለዷን የሚናገር እስካሁን አላገኘሁም፤ አስፈላጊ አይደለምና! የኔሰው ገብሬ የተናገረው፤ በነበረባት ኢትዮጵያ ያለው በደል፤ ለማንም ኢትዮጵያዊ የማይቻል መሆኑን ነበር። በተጨማሪ ረሃብና እርዛት በአንድ ወገን ሲደርስ፤ ወደ ሌላው አካባቢ በመሄድ ተጠግተዋል። ተመሳሳይ የባህልና የኅብረተሰብ ግንኙነቶችን መጥቀስ ይቻላል። እስኪ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፈጠረልንን ያካባቢ ማነቆ እንመርምር።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያበጀልን ያካባቢ ማነቆ፤

አሁን ችግራችን፤ ሀገሬን ነፃ አወጣለሁ የሚሉ ኢትዮጵያዊያና የኢትዮጵያን ክፍል አንድ ቆርጠው ነፃ አውጣለሁ በሚሉት መካከል ሊኖር የሚችል ግንኙነት ካለ፤ ምንድን ነው? የሚለው ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ለትግሬዎች ቆሜያለሁ እያለ ኢትዮጵያን እየገዛ ነው። አንዳንዶች ለትግሬዎች አዳላ እያሉ ማሰረጃቸውን በመደርደር ይናገራሉ። በትግራይ ያሉ ወገኖቻችን ደግሞ፤ የለም የራሳቸውን ቤተሰብና ዘመዶች እንጂ በሙሉ የትግራይን ወገን አልጠቀሙም ይላሉ። ማጣፊያው፤ ለእነዚህ መሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ጉዳያቸው እንዳልሆነ ነው። እዚህ ላይ የትግራይ ወገናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል በመሆናቸው የችግሩና የመፍትሔው ክፍል ናቸው። ይህ የሚያሳየን፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ለራሱና ለዘመዶቹ ጥቅም፤ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል መነሳቱን ነው። በየክልሉ ያስቀመጧቸው ተቀጥላዎቻቸው የግልና የዘመዶቻቸውን ኪሶች ማሳበጣቸው አብሮ የሚሄድ ነው። በኢትዮጵያዊነታችን የምናምን ደግሞ፤ የምንታገልለትን ማወቅና በግልፅ ማስቀመጥ አለብን። በተጨማሪም ከማን ጋር እንደምንሠለፍ መተለም አለብን። የራሴን ወገኖች ቆርሼ ነፃ ላወጣ ነው የሚል ግንባር፤ ከተቃዋሚ ኢትዮጵያዊያን ይልቅ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ይቀርበዋል። ሲመሽ ከዚህ ቡድን ጋር መቀላቀል ይቀለዋል። ምክንያቱም፤ ሁለቱም ላካባቢያቸው ጉዳይ ቅድሚያ ሠጥተው ነው በኋላ ኢትዮጵያን በያሉበት ተደራጅተው መቀላቀል የሚለው ትርጉም የሚሠጣቸው። ታሪካችን በደንብ መረዳት ከዚህ እንድንጠነቀቅ ይረዳናል።

ታሪክን በደንብ መረዳት ግዴታችን ነው፤

አሁን ባለንበት ዘመን፤ በተለይም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በፈጠረው የክፍፍል ቀመር እኛ ተመርዘን የቀድሞ አባቶቻችንና ነገሥታትን እንደኛ ያሰሉ ነበር የሚለው ጥሬ አስተሳሰብ ግንዛቤያችንን አሸውርሮታል። በቀድሞ መንግሥታት መካከል የነበረው አመዛኝ አመለካከት፤ ጠንካራ የሆነውን ወገን ማቸነፍ፤ ማቸነፍ ካልቻሉ ደግሞ በጋብቻ ማሰርና መዛመድ ነበር። ለዚህ ነው አጋዚ፣ አገው፣ አማራ፣ ትግሬና ኦሮሞ ነገሥታቶች የነበሩት። የዘር ግንዳቸውን በአባታቸው ቆጠሩት በናታቸው፤ ደማቸው የተደበላለቀ ለመሆኑ ማናችንም ልንጠራጠር አይገባም። በታሪክ የተመዘገበውን የነገሥታት የጋብቻ ትስስር ብናጤን፤ መዛመዱ ሀገር አቀፍ ነበር። ወደ ኋላ ራቅ ብሎ ማየት ይቻላል፤ እስኪ በዘመነ መሣፍንት ጊዜ በጎንደር ብንጀምር፤ ራስ አሊ ልጃቸውን ለካሣ ሲድሩ፣ ካሣ አማራ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ አላስገቡትም። ጠንካራ ጎበዝ መሆኑንና በጎናቸው ቢያሰልፉት እንደሚጠቅማቸው ተረድተው ነበር። አፄ ዮሐንስ የወሎውን ራስ አሊ ንጉሥ አድርገው በጋብቻ ሲጠምዱ ዘራቸውን አልቆጠሩም። አፄ ሚኒልክም ደግመውታል። አፄ ኃይለሥላሴም እንዲሁ። በትግሬ፣ በኦሮሞና በአማራ ነገሥታት መካከል፤ በግለሰብ ሥልጣናቸውን የሚያጠናክሩበትን መንገድ እንጂ፤ የደም ቁጥር ተሳስበው ያገለሉበት ወቅት ጎልቶ አይታይም። አሁን እኛ በገባንበት ማንቆ እነሱም ይግቡ ብለን የምናደርገው ትንንቅ፤ ብስለት የጎደለው የግንዛቤ ልልነት ነው። የትግራይ፣ የኦሮሞም ሆነ የአማራ ደም አላቸው ብለን ብንፈርጃቸውም፤ ነገሥታቱ ኢትዮጵያዊ ነበሩ። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪ የነበሩት፤ “የአክሱም ሐውልት ለወላይታው፤ የጎንደሩ ግንብ ለኦሮሞው ምን ያደርግለታል?” ያሉ ጊዜ፤ የሀገርን ምንነት ግንዛቤያቸውን ተረዳን። ይህ አባባል፤ በዘመነ መሣፍንት ጊዜ እንኳን፤ የራስን ኃይል ለማጠናከርና ወታደር ለመመልመል መሣሪያ ከመሆን አልፎ ትርጉም አልነበረውም። በአሁኑ ዘመን ሲነገር ደግሞ፤ ተናጋሪው ከዘመነ መሣፍንት በፊት መኖርና መሞት የነበረባቸው፤ ጊዜያቸውን አልፈው የተገኙ ተብለው እንዲወሰዱ ያደርጋል። ይኼን የመሰሉ መሪ ምን ዕቅድ እንዳላቸው ግልፅ ነበር። ከክልሉ ውጪ ያለው ማንኛውም ነገር የሱ አይደለም ማለት ነው። የአክሱም ሐውልት የአሁኑ የትግሬ ነዋሪዎች ነው ብሎ ማሰብ ታሪክን አለማወቅ ነው። ያኔ በዚያ ይኖሩ የነበሩት ማን እንደነበሩ ታሪክን ማገላበጥ ይረዳል። ያኔ በአክሱምና በጠቅላላው የሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል፤ ከአማሮችና ከትግሬዎች በፊት አብዛኛው ነዋሪ አገው እንደነበር ማስረጃዎች ብዙ ናቸው። በመካከላቸው በተደረጉት የጋብቻ ግንኙነቶች፤ የአገው ደም የሌለውን ኢትዮጵያዊ በዚህ ክፍል ማግኘት፤ የአማራ ደም የሌለበት ኢትዮጵያዊ ማግኘት፣ የኦሮሞ ዝንቅ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ማግኘት ቀላል አይደለም። የጎንደር ግንብም ሲሠራ ምን ያህል የኦሮሞ ባለሥልጣኖች በወቅቱ በዚያ ከተማ ይኖሩ እንደነበር ማገናዘብ ያስፈልጋል። አማራዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ኦሮሞዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ በተለያዩ ወቅቶች ኖረዋልና! ደም መቁጠሩ የት እንደሚያደርሰን በርጋታ እናስብ። የእኛ ኃላፊነት ምንድን ነው? እንመልከት።

ኃላፊነታችን፤

ኃላፊነታችን የነበረውን ታሪካችንን ተቀብለን፤ ከስኬቱ ሆነ ከስህተቱ ትምህርት ወስደን፣ የወደፊቱን ማስተካከል ነው። እኛ ለትናንቱ ሳይሆን ላለንበት ወቅትና ለነገው ሁኔታ ነው ተጠያቂነታችን። ኢትዮጵያዊ ነኝ ስንልና በኢትዮጵያዊነታችን ስንኮራ፤ በታሪካችን ሁሉም ጥሩ ሥራ እንጂ መጥፎ አልነበረም ብለን አይደለም። እኛ ኢትዮጵያዊ ስለሆን ብቻ ነው። መጥፎም ተደረገ ጥሩ፤ ታሪካችን ነው፤ ኢትዮጵያዊያን ነን። መጥፎ ስለተደረገ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፣ ዴሞክራሲያዊ መብቴ ስላልተከበረ ሀገሬ ለኔ ምን ታደርግልኛለች፣ የነበረው የኔ አይደለምና አዲስ መጀመር እፈልጋለሁ የሚለው ቁንፅልና ያልበሰለ ግንዛቤ ራሳችንን ጎጂ ነው። አንዳንዶች ከነገሥታቱ እየመረጡ አንዱን ኢትዮጵያዊ ሌላውን የአንድ አካባቢ ተጠሪ ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ አንዱን አረመኔ ጨፍጫፊ ሌላውን መልዓክ የሚያደርጉ አሉ። ኢትዮጵያዊነትን በአንገት ላይ እንደሚንጠለጠል ጌጥ አድርጎ መመልከት ጎጂ ነው። ኢትዮጵያዊነት የምንነት አካል ነው። ኢትዮጵያዊ ነኝ ወይንም አይደለሁም እንጂ፤ ኢትዮጵያዊነትን በኪሴ ያያዝኩት ንብረት ነው፤ ስፈልግ ባንገቴ አንጠለጥለዋለሁ አለያም ደብቄ በኪሴ እይዘዋለሁ የምንለው ጉዳይ አይደለም። በመሆንና ባለመሆን መካከል መቆሚያ አጥር የለም። ነህ ወይንም አይደለህም ብቻ ነው። እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ታሪካችን በብዙ ቢሆን ኖሮዎች የተሞላ ነው። አፄ ቴዎድሮስ እንዲህ ቢያደርጉ ኖሮ፣ በዚያ ቦታ እንዲህ ቢወስኑ ኖሮ፣ በዚያ ጊዜ ይኼን ባያደርጉ ኖሮ፣ . . . የምንላቸው ተትረፍርፈዋል። በአፄ ዮሐንስም ዘመን፣ በአፄ ሚኒሊክም ዘመን፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴም ዘመን። የሀገራችንን ታሪክ አጥፊዎቹ ሌሎች ናቸው እኛ አይደለንም ለማለት፤ እነሱ ይኼንን ባለማደረጋቸው ነው ወይንም ያንን በመድረጋቸው ነው እያልን፤ ሀገራችን ላለችበት ሁኔታ ወቃሾች ብዙዎቻችን ነን። እስኪ ከ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓመተ ምህረት ጀምሮ፤ ስንት አጎምዢ አጋጣሚዎች በዓይኖቻችን ሥር አልፈዋል? ይኼ ቢሆን ኖሮ፣ ያ ቢደረግ ኖሮ፣ . . . የምንላቸው ብዙ ናቸው። አሁንም ከመቼውም የበለጠ አጋጣሚ ከፊታችን ተዘርግቷል። ይኼን አጋጣሚ እንደሌሎቹ ሁሉ አሳልፈን፤ ለነገአዎቹ ቢሆን ኖሮ ካሳለፍንላቸው፤ በታሪክና በነገ ከተወቃሽነት አንወጣም። በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን በውስጡ በጣም የተወጠረበት ሰዓት ነው። አንዱ ሌሎቹን ገድሎ ብቻዉን በአቸናፊነት እንስኪወጣ ድረስ፤ በመካከላቸው ትርምስ አለ። ተቀምጠን እነሱ ተባልተው እንስጨርሱ ስንጠብቅ፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ሊገባ የሚችለውን ድል አስልፈን እንሠታለን። ተቃዋሚ ክፍሉ በአንድነት፤ የውስጥ መበላላቱን ትቶ፣ በአንድ አጀንዳ፣ በአንድ ድርጅት፣ በአንድ ራዕይ፤ ሥልጣኑንና ምርጫውን ለጠቅላላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትቶ፤ ከሕዝቡ ጎን ቢሠለፍ፤ የታሪክ፤ የትውልድና የሀገር ኃላፊነቱን ከመወጣት ሌላ፤ እያንዳንዳችን ልባችን ሞልቶ በፈገግታ ቀሪውን የሕይወታችን ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደእስካሁኑ ሁሉ ድርጅቶችን ቀድሞ ከፊት ቆሟል። እሁድ ግንቦት ፳ ፭ ቀን ፳ ፲ ፭ ዓመተ ምህረት የተደረገው ሰልፍ ትልቁ ምስከር ነው። የሰማያዊ ፓርቲ የጠራው ቢሆንም፤ ጠቅላላ ሕዝቡ የመራውና የሕዝቡ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ያን ያህል እንዳልነበሩ ዕውቅ ነውና! ስለዚህ ተጀምሯል። እኛ ተባበርንም አልተባበርንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደወሉን አስምቷል። ይልቁንስ በትልቁ የሀገራችን ጉዳይ እናተኩር። ኢትዮጵያዊ ሆነን እንቆጠር። እስኪ ሌሎች የራሳቸውን ታሪክ በተመለከተ ተመክሯቸውን እንመልከት።

የሌሎች ተመክሮ፤

በአሜሪካ መሥራች አባቶች በመባል የሚታወቁትን መሪዎቻቸው ብናጤን፤ በባርያ ፈንጋይነታቸውና ሠራተኛን በመበዝበዝ የሚታወቁት ባለፀጎች ነበሩ። ዛሬ እኒህ መሥራቾች በነጮችና በአፍሪካዊያን አሜሪካዊያን ዘንድ የማይነኩ ጣዖት ሆነዋል። እኛ የቀድሞ ነገሥታትን እንዴት ነው የምንመለከታቸው? ሪቻርድ ኒክሰን በአሜሪካ የስነ-አስተዳደር ቅጥፈት ተገኝቶባቸው፤ ከፕሬዘዳንትነት ተዋርደው የወረዱ መሪ ነበሩ። የሪቻርድ ኒክሰን የቀብር ስነ ሥርዓት ሲፈፀም፤ የነበረው ድምቀትና አዘኔታ፤ ልክ እንደ አንድ ታላቅ መሪ ነበር። መጥፎ ተግባራቸው የመሪነት የቀብር ስነ ሥርዓቱን አላጓደለባቸውም። ምን ጊዜም የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ነበሩ መባልን አያስቀረውም። ጆርጅ ቡሽ ለብዙ ሺህ አሜሪካዊ ወታደሮችና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኢራቅ ተወላጆች እልቀት ምክንያት የሆነውን የኢራቅ ወረራ በውሽት መረጃ አመካኝተው እዝ አስተላልፈዋል። አሜሪካ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ያካሄደችው ይህ ወረራ፤ ምንአልባት ቀጥሎ ለመጣው የምጣኔ ሀብቷ ቀውስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሳያደርግ አልቀረም። በዚህ ወረራ ከጠፋው ሕይወት ሌላ፤ የጠፋው ንብረት ቀላል አልነበረም። በተጨማሪም የሕዝቡን መብት በመጋፋት፤ ሕጋዊ ያልሆኑ ፍተሻዎችን፣ እስር ቤቶችን ማቋቋምና ግለሰቦችን ማሰር አከናውነዋል። ይኼን ሁሉ በአሜሪካን በዓለም ዙሪያ ለፈፀሙ መሪ፤ በአሜሪካ ውስጥ፤ ዳላስ ከተማ ከፈተኛ የሆነውን የቡሽ ቤተ መጽሐፍት ወዳጆቻቸው አቋቁመዉላቸዋል። እኛ የራሳችንን እንዴት እያየን ነው?

የዚህ ክፍል ማሳረጊያ፤

“ለየብቻችን ተማክለን እንጂ በአንድነት ተዋሕደን አንኖርም” የሚለውን ቅኝት ዘማሪዎች ከሁለት ወንዝ ይቀዳሉ። የመጀመሪያዎቹ በክፍፍሉ የራሳቸው ሥልጣን ስለታያቸው፤ ከግል የጥቅም ጉጉት አንፃር የሚያከሩ ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ ካለመፈለግም ሆነ ዕድሉን ስላላገኙ የማያውቁ ናቸው። በማንኛውም መንገድ ቢሆን ራሳቸውን ያላወቁ ናቸው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎችና ጸሓፊዎችን የሚያዙ ባለጉልበቶች ታሪካቸው እንደፍላጎታቸው እንዲተረክላቸው መጣራቸው አዲስ አይደለም። እኒህ ወገኖች ግን ሁሉን በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ ባለመቻላቸው፤ ታሪክ ከየቦታው እየሠረፀ በመውጣቱ፤ ተመራማሪዎች እያጠናቀሩ አቅርበውልናል። እናም በብዙ ድካም ከተለቃቀሙት ክፍሎች ታሪኩን መረዳት ችለናል። አሁን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የበላይ በሆነበት ወቅት፤ ይህ ቡድን የነበረውን ሆነ አሁን ያለውን በፈለገው እንዲቀረፅለት እየሞከረ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በሂደቱም ደግሞ የነበረውን ታሪክ መለወጥ የፈለገበት ምክንያት፤ አንድም የራሱን ሕልውና ሕጋዊና ዘለዓለማዊ ለማድረግ፤ ሁለትም የስነ ልቡና ለውጥ ለማምጣት ያለው ጥረት ነው። ስለተጻፈ ግን እውነት አይሆንም። የነበረው ነበር። አሁን ያለንበትን እንጂ የትናንቱን ሀቅ መለወጥ አንችልም። የትናንቱ ሀቅ ደግሞ፤ ትምህርት እንድናገኝበት ከተለያዩ ማዕዘናት መመርመርና መጠናት አለበት እንጂ፤ እንለውጠው ብሎ መነሳት፤ የአምባገነኖች ዓይነተኛ ባህርይ ነው። እኛ የምንታገለው በሀገራችን አሁን ያለው የአስተዳደር ጉድለት፤ ከዕርማት በላይ ስለሆነ መለወጥ አለበት ብለን ነው። ስለታሪካችን የታሪክ ተመራማሪዎች በመስካቸው እንዲከራከሩበት ነፃነቱ እንዲሠጣቸው እንታገልላቸው። ስላሁን ነፃነታችን አሁን እንታገላለን።


የኢትዮጵያዊያን ትግል – ( ክፍል ሶስት )

የሁለት ደረጃ ትግላችን፤

በዚህ ርዕስ በተከታታይ በቀረበው ባሁኑ የሶስተኛው ክፍል፤ በቀጥታና በግልፅ ቋንቋ ምን ማድረግ እንዳለብን አብራራለሁ። በመጨረሻውና አራተኛው ክፍል ደግሞ ከዚህ ወዴት? በሚል መዝጊያን አቀርባለሁ። ኢትዮጵያዊያን አሁን ባለንበት የፖለቲካ ሀቅ፤ ሁለት ደረጃ ያለው ትግል ማድረግ የግድ አለብን። እኒህን በቅደም ተከተል መደረግ ያለባቸው ትግሎች፤ በግልፅ ተረድተንና ተከትለን ካልሄድን፤ ትግላችን የእሬያ ታጥቦ ጭቃነት ነው። እኒህ ትግሎች በፊታችን የተጋረጡ ለመሆናቸውና የግድ ማድረግ ያሉብን ለመሆናቸው፤ ማናችንም ብንሆን ጥርጣሬ የለንም። አንጥረን የለየናቸውና በዚያ ስሌት ያስቀመጥናቸው ለመሆናቸው ግን፤ ጥያቄ አይጠፋም። እንዲያውም ዝብርቅርቅ ያለ ጭጋግ ወጥሮ ይዞናል። ይህን ለማሳየት መጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን ያለንበትን ሁኔታ እንመልከት።

ኢትዮጵያዊያንን የማይወክል መንግሥት አዲስ አበባ ላይ ተቀምጧል። ይህ መንግሥት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ አስቀድሞ፤ ሀገራችንን ከአንድነት ወደ ልዩነት በመንዳት፤ ለርስ በርስ ትልቅልቅ እያዘጋጀን ነው። በውልድ ኢትዮጵያዊ ይሁኑ እንጂ በተግባር ፀረ-ኢትዮጵያዊ ለመሆናቸው መረጃ የሚጠይቀኝ የለም። ግልፅ ነውና! በእርግጥ እስካሁን በተለያዩ ወገኖቻችን መካከል መጠፋፋቱ አልተከሰተም ብዬ አይደለም፤ መጪው መለኪያ የሌለው የከፋ መሆኑን ለመጠቆም ነው። ድህነቱ፣ በበሺታ ማለቁ፣ ያልተመጣጠነ አስተዳደርና እድገት በተለያዩ ቦታዎች መከሰቱና መደልበቱ፣ የአስተዳደር በደል ጣራ መንካቱ፣ የኑሮ ውድነቱ ማሻቀቡ፣ . . . ወዘተ፤ ባጠቃላይ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ መሄዱ የተዘገበ ነው። ይኼን እንደ አስተዳደር ብልጠት የተሞሽረበት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት፤ በዕብሪትና ባለው አቅም እየገፋበት ነው።

በተጓዳኝ የተቃዋሚዎቹን ወገን የተመለከትን እንደሆን ደግሞ፤ አንድ ማዕከል የሌለው፣ አንድ የትግል ራዕይ የሌለው፣ እጅግ በጣም የተበታተነ ክፍል እናያለን። በነዚህ የተለያዩ የተቃዋሚ ወገኖች ውስጥ፤ እጅግ በጣም ቆራጥና ሕይወታቸውን ለወገናቸውና ላገራቸው ለመሥጠት ወደ ኃላ የማይሉ ታጋይ ወጣቶች ሞልተውባቸዋል። የአብዛኛዎቹ የነዚህ ወጣቶች ፍላጎት፤ የኢትዮጵያዊያን ነፃነት፣ የሀገራቸው ብልፅግናና እድገት ብቻ ነው። እነዚህ ወጣቶች፤ ማን ነገ በሕዝቡ ተመርጦ መሪ ይሆናል? ማን ይቸነፋል? የሚሉት በአእምሯቸው ቦታ የላቸውም። በመሪዎቻቸው በኩል የተገላቢጦሽ ነው። አሁንም እነኚህ ወጣቶች በአንድነት ለኢትዮጵያ ለመሠለፍ ዝግጁ ናቸው። መሪዎቻቸው ግን አጥር አበጅተውባቸዋል። የነሱ ድርጅት፣ የነሱ ፍልስፍና፣ እነሱ አጥቂና የበላይ ካልሆኑ፤ ትግሉ አፍንጫውን ይላስ ያሉ ይመስላሉ። እናም “ሌሎቹ ስህተተኞች ናቸው”ብለው ይስብኳቸዋል። ይህ ሊፈርስ የሚችለውና ባንድ ላይ ተሰባስበን ልንታገል የምንችለው፤ የትግሉን ምንነትና መንገድ በአደባባይ ተወያይተንበት ግልፅ ግንዛቤ ስንይዝ ነው። በዚህ ለይስሙላ የተዘረጉት አጥሮች በሙሉ ይፈራርሳሉ። ለዚህም ነው አሁን ካለንበት የፖለቲካ አረንቋ ወጥተን ነገ ትሆን ለምንፈጋት ኢትዮጵያ መንገዱ ሁለት ደረጃ ያለው ትግል ነው የምለው። የተጋዮች በአንድ ወገን መሠለፍ ግዴታ ነው። እነሆ ሁለቱ የትግል ደረጃዎች።

ሁለቱ የትግል ደረጃዎች ምንድን ናቸው?

መልካም። በሁለቱም የትግል ደረጃዎች ውስጥ የአስተሳሰብና የሃሳብ ልዩነቶች አሉ። የሚለያዩበት ቢኖር፤ እንዴት ይስተናገዳሉ በሚባልበት ጊዜ የሚሠጣቸው መፍትሔ ላይ ነው። የመጀመሪያዉን ከመዘርዘሬ በፊት ሁለተኛውን ማስቀደሙ፤ ለግንዛቤ ይቀላልና በሱ ልጀምር።

ሁለተኛው የትግል ደረጃ፤

የሁለተኛው የትግል ደረጃ፤ የእኔ አምራለሁ፣ እኔ አምራለሁ፣ ውድድር ነው። በኔ አምራለሁ አኔ አምራለሁ ውድድር፤ ከፈራጅ ፊት ቀርቦ መልስ መጠበቅ እንጂ፤ እርስ በርስ ማማርን ለማሻሻል ሆነ ለማሳየት ፍጥጫ የለበትም። የሌላውን አለማማር ለማሳደግ ሲሮጡ የራስንም አለማማር ስለሚያባብሱት ሁሉም በዚያ ጎዳና መጓዙን አይወድም። ከጎኑ ያለውን እንዳያምር አደርጋለሁ ብሎ የሚነሳ፤ የራሱ አለማማር ከመጉላቱ ሌላ፤ ያልተነኩት ማማራቸው ወደ ላይ ስለሚወጣ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ይሆናል። እዚህ ላይ አምራለሁ ባዮች የፖለቲካ ድርጅቶች ፈራጅ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ትግሉም የሰላምና የሃሳብ ትግል ነው። እንግዲህ በዚህ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ፤ የርዕዩተ ዓለም ልዩነት በሕዝቡ ፊት እየቀረበ፤ የምንፋረጅበት ነው ማለት ነው። የዴሞክራሲ ትግል ነው። ሕጋዊ ትግል ነው። ሕጉም የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ነው። በሀገሪቱ ያለው መንግሥት ከተወዳዳሪዎቹ የተለዬና ነፃ የሆነ ነው። እናም በመንግሥቱና በወቅቱ የመንግሥቱን በትር በጨበጠው የፖለቲካ ድርጅት መካከል ግልፅ የሆነ ልዩነት አለ። ይህ እንግዲህ የዴሞክራሲያ አሠራር የሠፈነበት ኅብረተሰብ መኖሩን ያሳያል። ይህን አሠራር የሚያራምዱትና የሚጠብቁት፤ ሕገ መንግሥቱ፤ መንግሥታዊ መዋቅሩና እያንዳንዱ የሀገሪቱ ዜጋ ናቸው። በዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ፤ ወደ ኋላ የመጓዝ ዕድሉ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል ባይባልም፤ በጣም ጠባብ ነው። መብቱን በተረዳ ሕዝብ መካከል፣ ይኼንን መብት በግልፅ ያስቀመጠ ሕገ መንግሥት ባለበት ሀገርና መንግሥታዊ መዋቅሩ ለዚህ አመቺ ሆኖ በተዘረጋበት እውነታ፤ አምባገነኖች የመፈልፈላቸውና ፍላጎታቸውን በሕዝቡ ላይ የመጫናቸው ዕድል የጠበበ ነው። በዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ግን ትልቅ አጥር መሻገር ይኖርብናል። ይኼውም የመጀመሪያው ትግል ነው። የመጀመሪያውና አስቸጋሪው ትግል በቅድሚያ መደረግ አለበት።

የመጀመሪያው ትግል፤

ከላይ ባስቀመጥኩት የሁለተኛው ትግል፤ የተለያዩ አመለካከቶች ያሏቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አመለካከታቸውን በሕዝብ ፊት በማቅረብ፤ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚወዳደሩበት እንደሆነ አሳይቻለሁ። ይኼኛው የመጀመሪያው የትግል ደረጃ ከዚያኛው የትግል ደረጃ በጣም የተለዬ ነው። እዚህ ላይ የርስ በርስ ውድድር የለበትም። ይኼ መሠመር አለበት። እዚህ ላይ የርስ በርስ ውድድር የለበትም። ፈራጅ የለም። እዚህ ላይ የኢትዮጵያዊያን የሕልውና ትግል ነው። ይህ ወደ ሁለተኛው የትግል ደረጃ ለመድረስ ጠራጊ ትግል ነው። ይህ እኔ አምራለሁ እኔ አምራለሁ በማለት የሚኮፈሱበት ሳይሆን፤ ለመጠፋፋት የሚነሱበት የትግል ደረጃ ነው። በእርግጥ፤ እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ምርምር ሁሉ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው ማለት አልችልም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪዎች፤ “ሳንጠፋፋ አብረን እንሥራ ብለው”ሊሠለፉ ይችላሉ ብሎ የሚሞግተኝ እንደማይጠፋ እርግጠኛ ነኝ። እስኪ እኒህን እንመልከታቸው።

በኔ በግል አመለካከቴ፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው ቅራኔ የመጠፋፋት ደረጃ ለይ ስለደረሰ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን የሚያገኘው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥትን አወድሞ ነው እላለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የለም መጠፋፋቱ አያስፈልግም፤ ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት፤ ሀገራችን ያለችበትን አደጋ ተረድቶ፣ ፈቃደኛ ሆኖ፣ ከተቃዋሚዎቹ ጋር በመተባበር፣ የዴሞክራሲያዊ አሠራርን ተቀብሎ፤ የሽግግር መንግሥት ይመሠርታል የሚሉ አሉ። አይሆንም ብዬ አልከራከራቸውም። የሚሆንበት መንገድ የለም ብዬም ደረቅ አቋም አልወስድም። የመሆን ዕድል አለው። እኔ ግን በሕልሜም አይመጣልኝም። እናም አላምንም። አሁንም በትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያው ትግል፤ የጠፊና የአጥፊ ነው እላለሁ። በዚህ ጎን የሚሠለፉ፤ ቅኝ ተገዢዎችና የቅኝ ገዢዎች፣ ተወራሪዎችና ወራሪዎች፤ ትክክለኛ የሆነና ትክክለኛ ያልሆነ ጦርነት አነሳሾች ናቸው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ትክክለኛ የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሕጋዊ አይደለም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መሪ ሆኖ ከቀጠለ፤ ሀገራችንን ያጠፋታል። ይኼንን እያልኩ፤ ከዚህ መንግሥት ጋር የሰላም ድርድር ይቻላል የሚል ብዥታ አላራምድም። ኢትዮጵያዊያን ለሕልውናችን ስንል ይኼን መንግሥት ማስወገድና ማጥፋት አለብን። የለም ይህ መንግሥት መጥፋት የለበትም የሚሉ ደግሞ፤ ሀገር ውስጥ በሚደረገው ሕጋዊ ትግል ገብተው፤ በሰላማዊ መንገድ፤ ትክክለኛ መንግሥት ለመመሥረት መታገል አለባቸው። ይህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተደምስሶ ኢትዮጵያዊ መንግሥት መመሥረት አለበት ባዮች ደግሞ፤ ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆነ የሚባል ትግል የለንም። የትኛው ሕግ? ማንኛውንም መንገድ በመከተል መታገል አለብን። በአንዳንዶች ዘንድ ሰላማዊ ያልሆነ ትግል መልሶ ሌላ አምባገነን ስለሚያመጣ፤ የትጥቅ ትግል ቦታ የለውም የሚሉ አሉ። ለዚህ እኮ ነው ውይይት አድርገን፤ ሀገር አቀፍ የሆነ አንድ ድርጅት ብቻ መሥርተን፤ በማንኛውም መንገድ እንታገል የምለው። የሚያስፈራው ሰላማዊ ወይንም ትጥቃዊ መሆኑ አይደለም። የሚያስፈራው አንድ የራሱ የሆነ ጉልበታም ድርጅት፤ ሌሎቹን ሁሉ ጠቅጥቆ፤ በራሱ አጀንዳ አዲስ አበባ ላይ የተፈናጠጠ እንድሆነ ወይንም ጠመንጃውን ተመክቶ፤ ተገንጥሎ የሄደ እንደሆነ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን፤ አንድነት ያለውና አንድ ብቻ ኢትዮጵያዊ ኃይል፤ በማንኛውም መንገድ ሊጥለው ግዴታ አለብን። የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው። ስለዚህ፤ የታጠቀ አመፅ ለሚያስፈራችሁ፤ አትፍሩ፤ ኢትዮጵያዊና መላ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚሉ ኢትዮጵያዊያንን ያካተተ ስለሚሆን፤ መቼ ደርሶ በሉ! በነገራችን ላይ ስለትግሉ ጥቅል መልክ ለመሥጠት እንጂ ዝርዝሩን በሚመለከት ገና አልጀመርኩም።

የመጀመሪያው ደረጃ ትግል ዝርዝር፤

እንዲህ ነው። ኢትዮጵያዊያን ለሕልውናችን የምናደርገው ትግል አንድ አጀንዳ፣ አንድ መልክ፣ አንድ ማዕከልና አንድ ግብ  ብቻ ነው ሊኖረው የሚገባ። የተለያዩ ማዕከሎች ካሉት፤ ሌላ ትግል በመካከላችን እያዘጋጀን ነው ማለት ነው። አንድ ማዕከል ካላደረግን፤ ተጠፋፊዎች የሆኑ አካላት በመካከላችን አሉ ማለት ነው። ከሁለተኛው ደረጃ ከመድረሳችን በፊት መጠፋፋት ያለብን ክፍሎች አለን ማለት ነው። ይሄ ከታወቀ፤ አጥፊና ጠፊ ባንድ ስለማንሠለፍ፤ ሠፈራችንን ካሁኑ ለይተን መደራጀት አለብን። በዚህ የሕልውና ትግል አንድ ማዕከል ብቻ ሳይሆን አንድ ድርጅት ብቻ እንዲኖር ግዴታ አለ የሚል ነው እምነቴ። ለምን ቢባል፤ የዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫዬን ነውና! መለያየታችን በሀገር ሕልውና ከሆነ ካሁኑ እንጠፋፋ። የምንለያየው በዴሞክራሲያዊ እምነታችን የመፍትሔ መንገድ ከሆነ በኋላ ከሕዝብ ፊት ስንቀረብ ፈራጁ ስለሚያስተናግደን፤ ቅደም ተከተላችንን እንወቅ። ትግላችን ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት ብለን ነው። ትግላችን ኢትዮጵያዊያን ነን ብለን ነው። ትግላችን የሕግ የበላይነት በሀገራችን ይኑር ብለን ነው። ትግላችን የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብት በትክክል ይከበር ብለን ነው። ትግላችን የሀገራችን ዳር ደንበር ይጠበቅና ይከበር ብለን ነው። ትግላችን የኢትዮጵያዊያን አንድነት ይኑር ብለን ነው። ትግላችን ለዚህ ሁሉ ስኬት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ተወግዶ የኢትዮጵያዊያን መንግሥት ይቋቋም ብለን ነው። በዚህና ለዚህ የምንሰባሰበው ደግሞ፤ እያንዳንዳችን በየኪሶቻችን በያዝናቸው ዘውዶች ልክ የተሰፋ ድርጅት ይዘን በመሰለፍ አይደለም። የግድ አንድና አንድ ድርጅት ብቻ ይዘን ነው። ለዚህ ትግላችን ከአንድ በላይ ድርጅት አፍራሽ ነው። ለምን? ከላይ የተዘረዘሩትን የትግል ዕሴቶቻችንን በአንድ ድርጅት ለማሳካት መነሳት አለብን። ከነዚህ አንዷንም አልቀበልም ያለ የትግሉ አካል አይሆንም። በእርግጥ መጨመር ይቻላል፤ ቁም ነገሩ ግን ሁላችንን የሚያስማሙ መሠረታዊ የትግል ዕሴቶችን በመለየት ላይ ነው። በነዚህ ላይ እንስማማለን የሚል እምነት አለኝ።

የሕልውና ጥያቄ ያለው አንድ መልስ ብቻ ነው። መኖር ወይንም አለመኖር። መኖር ደግሞ አንድ ሕይወት ነው ያለው። የኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ መኖር አንድ ነው። የኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ መኖር ሁለትና ሶስት የለውም። አለን ወይንም የለንም ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ አለች ወይንም የለችም ነው። እንድንኖር ደግሞ በአንድነት አለን ለማለት እንድንችል በአንድነት መሠለፍ አለብን። የአኗኗራችንን ሁኔታ፤ ሕይወታችንን ስናረጋግጥ እንነጋገርበታለን። መጀመሪያ ግን ሕልውናችንን እናረጋግጥ። ይህ ማለት ደግሞ፤ ለሕልውናችን አንድ ሆነን በአንድነት እንታገል ማለት ነው። ታዲያ ሁለትና ሶስት ድርጅቶች፣ ሁለትና ሶስት ማዕከሎች፣ ሁለትና ሶስት የአመራር መዋቅሮች ተልዕኳቸው ምንድን ነው? በእርግጥ ይኼ ቀላልና ግልፅ በሆነ መንገድ ስንመለከተው ነው። ለአንዳንዶች የነበራቸው ታሪክ፣ የከፈሉት መስዋዕትነትና የድርጅታቸው ጥንካሬ እየጎተታቸው ይኼንን መቀበል ይገዳቸዋል። ቁም ነገሩ ግን፤ የተዋደቁለት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነቱን አግኝቶ የራሱ ምርጫ እንዲኖረው እንጂ፤ የነሱ ድርጅት የግድ የበላይ ሆኖ ገዢ እንዲሆን አልነበረምም፤ አይደለምም። እንግዲህ እዚህ ላይ፤ በትክክለኛ መንገድ ድርጅታቸውን የትግል መሣሪያ አድርገው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታግለውበታል ከሚለው ቅን አስተሳሰብ በመነሳት ነው። በያዙት ርዕዩተ ዓላማ ጠንካራ እምነት ካላቸው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እምነት ካላቸው፣ ያደረጉት ተጋድሎ የሕዝብ ነው ብለው ካመኑ፤ የድርጅታቸውን ጉዳይ በሁለተኛው የትግል ደረጃ ለማምጣት የሚያግዳቸው የለም። በሌላ በኩል ደግሞ፤ አባሎቻቸው በድርጅቶቻቸውና በርዕዩተ ዓለሞቻቸው ሙሉ እምነት ያላቸው ከሆኑ፤ ድርጅቱ በሰዓቱና በቦታው ሲመሠረት መምጣታቸው አይቀርም። አለያ ፍርሃት አለ ማለት ነው! ያንን ራሳቸው ይመርምሩ። በብልጠት ቦታ መያዣ አድርገው፣ ካሁኑ መረቦቻቸውን ዘርግተው፣ ድርጅታቸውን አጠናክረው፣ የተጠራቀመ ድልብ ሆነው ለሥልጣን ከሆነ ድርጅታቸውን የሚፈልፉት የሕዝብ ክፍል ለመሆናቸው ጥርጣሬ እንዳሳድር ያደርገኛል። ትግሉ ሕዝቡን የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ እስከሆነ ድረስ፤ ቅንነት፣ ቆራጥነት፣ መስዋዕትነት፣ እና ከራስ ወዳድነት የራቀ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚጠበቀው ከታጋዮች። በተለይም የተሰው ታጋዮችን የትግል ፍሬ መቁጠር ያለብን በሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤትነት መሆን አለበት።

ከዚህ ወዴት?

ከዚህ በላይ በሠፈሩት ከተስማማን፤ መስማማታችንን መጀመሪያ ማስመር ግድ ነው፤ ቀጥሎ ምን ይደረግ ወደሚለው እንሄዳለን። ነገር ግን፤ ከላይ የሠፈረው ቀላልና እንዲያው ባድ ሰው ጽሑፍ ወይንም ባንድ ምሽት የሚካተት ስላልሆነ፤ ሁላችን በያለንበት እንድናብላላውና የየራሳችን የሆነ አቋም ወስደን እንድንወያይ፤ ጊዜ መሥጠት እፈልጋለሁ። ይኼ የኔ የብቻዬ ወይንም የግሌ ጉዳይ አይደለም። ጉዳዩ የሀገራችንና የሁላችን ነው። ያቀረብኩት የራሴን አቋም ነው። ከኔው የተሻለ ሃሳብ ሊኖር ይችላል። ጥሩ የሚሆነው፤ የለም እንዲያ አይደለም፤ ተሳስተሃል ተብዬ የናንተን ደግሞ ባዳምጥ ስለሆነ፤ ተነጋገሩበት። የሀገር ጉዳይ በአደባባይ እንዲህ ወጥቶ ብንነጋገርበት፤ ወደ ጥሩ መፍትሔ አንሄዳለን። ከዚህ ወዴት? የሚለውን በሚቀጥለው አራተኛውና የመጨረሻው ክፍል አቀርባለሁ። (ክፍል አራት – የመጨረሻው ይቀጥላል)

 golgul.com

Advertisements

Posted on July 4, 2013, in News and tagged , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s